የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር አጋርነት ለቀጣናዊ ሰላም እና የጋራ ዕድገት
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘትና በቀይ ባሕር ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን በአካባቢው ብሎም በቀጣናው ሰላምን ለማስጠበቅ እንዲሁም ለቀጣናዊ ትስስር እና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡
ቀይ ባሕር አፍሪካን ከእስያ እና ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር የሚያገናኝ ስትራቴጂካዊ የንግድ መስመር ቢሆንም ከፍተኛ የባህር ላይ ውንብድና፣ ህገ ወጥ የሰዎች እና የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም ግጭቶች የሚካሄድበት አካባቢ ነው፡፡
በዚህ መልኩ በቀይ ባሕር ላይ የሚካሄዱ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣናው ሀገራት ላይ አሉታዊ ጫና እና የብሔራዊ ደህንነት ስጋት የማስከተል ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡
ለአብነትም አል ሻባብን ጨምሮ ሌሎች ወሰን ተሻጋሪ አሸባሪ ቡድኖች በቀይ ባሕር አካባቢ መንቀሳቀሳቸው የቀጣናው ሀገራት ችግሩን ለመከላከል በጋራ የሰላም ማስከበር እና ህገወጥ እንቅስቃሴን የመከላከል ተግባር እንዲያከናውኑ ያስገድዳቸዋል፡፡
በተመሳሳይ አካባቢው ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ባህር በሚያቋርጡ ፍልሰተኞች ላይ የከፋ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሚፈፅሙበት ነው፡፡ ከአካባቢው ሀገራት የሚነሱ ህገወጥ ስደተኞች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለማቋረጥ በሚሞክሩበት ወቅትም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጀልባ መስጠም አደጋ ሰለባ ሆነዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷ ለቀጣናው ሀገራት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ቀይ ባሕር ከውድድር ይልቅ የትብብር ቀጣና እንዲሆን ከማስቻሉ ባሻገር የባሕር ላይ ውንብድና፣ ሽብርተኝነት፣ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ እና ሰዎች ዝውውር ድንበር ዘለል ችግሮችን በጋራ ለመቀነስ ከፍ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከባሕሩ ከ60 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው ኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የህዝብ ቁጥሯ እና ኢኮኖሚዋ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናው ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ ትብብርና መሰረተ ልማት መስፋፋት ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡
ሀገራት በንግድ፣ በመሠረተ ልማትና በኢኮኖሚ በተሳሰሩ መጠን ደግሞ ከግጭት ይልቅ ትብብርን የመምረጥ ዕድላቸው እንደሚጨምር የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በመሆኑም የመደመር መንግሥት የባሕር በር ጥያቄን በተመለከተ ቁርጠኛ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን ጥያቄው በበርካታ ሀገራት እና ተቋማት ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል፡፡
በመሆኑም የቀጣናው ሀገራት ይህንን የኢትዮጵያን ፍትሃዊና ህጋዊ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ ያገኝ ዘንድ ድጋፍ ማድረግ ምክንያታዊ ተግባር ነው፡፡
በሚኪያስ አየለ