የኢትዮጵያና አሜሪካ ወታደራዊ ትብብር ወደ ስትራቴጂያዊ ደረጃ ተሸጋግሯል – አይሻ መሃመድ (ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለው የዲፕሎማሲና የወታደራዊ ትብብር ወደ ስትራቴጂያዊ ደረጃ ተሸጋግሯል አሉ፡፡
ሚኒስትሯ በአዲስ አበባ በተጀመረው የ2026 የአፍሪካ ኮሙኒኬሽንና ሎጂስቲክስ ሲምፖዚዬም መክፈቻ ላይ እንደገለጹት÷ ይህ እድገት በሁለቱ ሀገራት መካከል እየጠነከረ የመጣውን የመተማመንና የአጋርነት ግንኙነት የሚያሳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዚህ ትልቅ አህጉራዊ መድረክ አስተናጋጅ ሆና መመረጧ ሀገሪቱ ለቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ፣ የተመዘገበውን የልማት ውጤትና የአዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን የማስተናገድ አቅም የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል፡፡
ለሲምፖዚዬሙ ስኬታማ ዝግጅት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የአሜሪካ አጋር ተቋማት አመራሮችና አዘጋጆች ምስጋና አቅርበዋል።
አፍሪካ በተወሳሰቡ የደኅንነትና የሰብዓዊ ተግዳሮቶች እየተፈተነች ባለችበት ወቅት ጠንካራ የሎጂስቲክስ ሥርዓትና የተቀናጀ የመገናኛ አቅም፣ የወታደራዊ ዝግጁነት፣ የተቀናጀ እንቅስቃሴና ፈጣን ምላሽ ወሳኝ መሠረቶች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ሲምፖዚዬሙ የቴክኒክ ውይይት መድረክ ብቻ ሳይሆን አጋርነትን ለማጠናከር፣ ልምዶችን ለመለዋወጥ፣ በፈጠራ ላይ በመመስረት በመላው አፍሪካ ብቁና ዘመናዊ ተቋማትን ለመገንባት ጠቃሚ አጋጣሚ መሆኑን አመልክተዋል።
በቀጣዮቹ ቀናት ተሳታፊዎች ከዛሬ ተግዳሮቶች ባሻገር በማሰብ ለወደፊቷ አፍሪካ የሚያስፈልጓትን ስትራቴጂያዊ አቅሞች በጋራ እንዲገነቡ ጥሪ አቅርበዋል።
አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) የ2026 የአፍሪካ ኮሙኒኬሽንና ሎጂስቲክስ ሲምፖዚዬምን በይፋ ከፍተዋል።
በመሳፍንት ብርሌ