የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የ2019 በጀት 45 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ሆኖ ጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት 45 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በጀት አጽድቋል።
የክልሉ ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ የኋላሸት በላይነህ በታርጫ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ላይ የበጀት ሪፖርቱን አቅርበዋል፡፡
ከአጠቃላይ በጀቱ የክልሉ መንግሥት ከመደበኛ፣ ከማዘጋጃ ቤትና ከሌሎች የውስጥ የገቢ ምንጮች ከ29 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የሚሸፍን ሲሆን፥ ቀሪው 16 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ከፌዴራል መንግሥት ድጎማ፣ ከዘላቂ ልማት ግቦችና ከውጭ እርዳታ ይሸፈናል ብለዋል፡፡
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ተመስገን ከበደ በበኩላቸው፥ በጀቱ ለድህነት ቅነሳ ዘርፎች ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ማህበራዊ አገልግሎትን ለማጠናከር፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ የኢንዱስትሪና የኤክስፖርት ምርቶች እንዲሁም መስኖ ልማትን ጨምሮ የግብርና ስራዎችን ለማስፋትና ለፕሮጀክቶች ማጠናቀቂያ የሚውል መሆኑን አመላክተዋል።
ምክር ቤቱ በቀረበው የክልሉ የ2019 ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።