Fana: At a Speed of Life!

ሻዕቢያ ሕዝቡን ለእንግልትና ለስደት ዳርጓል፤ ኢትዮጵያ ከ400 ሺህ በላይ ኤርትራውያንን ተቀብላ አስጠልላለች

ሻዕቢያ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ከ30 ዓመታት በላይ በኤርትራ ሕዝብ ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን አስከትሏል፡፡
የኤርትራ ሕዝብ ከሰላሳ ዓመታት በላይ በተደረገ የትጥቅ ትግል ነጻነት ተጎናጸፍኩ ቢልም፣ የነጻነት ትግሉን የመራው የሻዕቢያ መንግሥት፣ ሀገሪቱን በብቸኝነት እያስተዳደረ ይገኛል።
ይህ አካሄድም ኤርትራን ወደ ተወሳሰበ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የከተታት መሆኑን ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው የመጡ ኤርትራውያን፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የፖለቲካ ተንታኞች ይስማማሉ።
በኤርትራ የሚታየው ዋነኛው ቀውስ ከፖለቲካዊ መዋቅሩ ጋር የተያያዘ ነው። በፈረንጆቹ 1997 የሀገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ያጸደቀውና በርካታ የሲቪል መብቶችን የያዘው ህገ-መንግሥት እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አልተደረገም፡፡
በሀገሪቱ ውስጥ የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ነው ያለው፡፡ ከሻዕቢያ ውጭ ሌላ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይቋቋም በህግ የተከለከለ ሲሆን፣ ሀገራዊ ምርጫም ተካሂዶ አያውቅም።
ከፈረንጆቹ 2001 ጀምሮ የግል መገናኛ ብዙሃን ሙሉ በሙሉ የተዘጉ ሲሆን÷ መንግሥትን የተቹ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ጋዜጠኞችና የሃይማኖት መሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በእስር ላይ ይገኛሉ።
ለሥርዓቱ ታግለው በእስር ላይ ሕይወታቸውን ያጡም በርካቶች ናቸው፡፡
ህግ አውጪ፣ ህግ ተርጓሚና ህግ አስፈጻሚው አካል በአንድ ግለሰብ ማለትም በኢሳያስ አፈወርቂ ቁጥጥር ሥር መውደቃቸው የፍትህ ሥርዓቱን አዳክሞታል።
የኤርትራ መንግሥት ራስን መርህ ያደረገ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እከተላለሁ ቢልም በተግባር ግን ኢኮኖሚው እንዲዳከምና የሕዝቡ የመግዛት አቅም እንዲደቅ አድርጓል።
የግሉ ዘርፍ እጅግ የተገደበ ሲሆን÷ አብዛኛው የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሻዕቢያ የንግድ ተቋማትና በጦር አዛዦች ቁጥጥር ስር ነው። ይህ የመንግሥት ሞኖፖሊም ጤናማ የገበያ ውድድር እንዳይኖር አድርጓል።
በፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ በሕግ የበላይነት እጥረትና በውጭ ምንዛሪ ቁጥጥር ምክንያት የውጭ ሀገር ኩባንያዎች በሀገሪቱ ኢንቨስት ማድረግ አይፈልጉም።
በሀገሪቱ የተጠናከረ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ባለመኖሩ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ደርግ ጥሏቸው እንደሄደ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናው በቀጥታ የኤርትራን ህዝብ ስነ-ልቦናዊና ሥነ-ሕዝባዊ መዋቅር አናግቶታል።
የግጭት ስነልቦና ያልተለየው ሻዕቢያ፣ ወጣቶች በውትድርና እንዲያገለግሉ ግዴታ ይጥላል፡፡
ወጣቶችም በሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ስልጠናቸውን ከጨረሱ በኋላ ለዓመታት በዝቅተኛ ክፍያ በውትድርናና በግዳጅ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ይደረጋል። ይህ አሰራር የወጣቶችን የወደፊት ተስፋ ያጨለመ ሆኗል።
ከዚህ የግዳጅ አገልግሎትና ከኢኮኖሚ ችግር ለማምለጥ በየወሩ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ይሰደዳሉ። ይህ ስደት ሀገሪቱን የተማረና አምራች የሰው ኃይል አሳጥቷታል።
አባወራዎች በውትድርና ረጅም ጊዜ ማሳለፋቸውና የወጣቶች በብዛት መሰደድ የኤርትራውያንን ማህበራዊ ትስስርና የቤተሰብ መዋቅር እያፈራረሰው ይገኛል።
ከኤርትራ መገንጠል በኋላ በሀገሪቱ ካለው የፖለቲካና የግዳጅ ውትድርና ሥርዓት ለማምለጥ በ100 ሺህ የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ተሰደዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በርካታ ስደተኞችን ከሚያስተናግዱ ግንባር ቀደም ሀገራት አንዷ ስትሆን÷ የኤርትራ ስደተኞች ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ ቀጥሎ ሦስተኛውን ትልቅ ስብስብ ይይዛሉ።
የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ተመሳሳይ የስነ ልቦና ውቅር፣ ታሪክ፣ ባህልና ኃይማኖት የሚጋሩ ህዝቦች በመሆናቸው፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ400 ሺህ በላይ የኤርትራ ስደተኞችን አስጠልላ ትገኛለች፡፡
ይህ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ዜጎች የምታደርገውን ሰብዓዊ መስተንግዶ የሚያሳይ ሲሆን÷ ኤርትራውያንን ጨምሮ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ስደተኞች መጠለያ ናት፡፡
በአጠቃላይ ሻዕቢያ ኤርትራን ወደ ተሻለ የዴሞክራሲና የብልጽግና ምዕራፍ ማሸጋገር አልቻለም። ሻዕቢያ እነዚህን ቀውሶች ከራሱ የፖሊሲ ስህተት ይልቅ ከውጭ ሀገራት ጫና፣ ከድንበር አለመወሰንና ከዓለም አቀፍ ማዕቀቦች ጋር ለማያያዝ ይሞክራል፡፡
በሀገር ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን የሕዝቡን ህይወት እጅግ ፈታኝ አድርጎታል።
ኤርትራ ካለችበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንድትወጣ፣ የአንድ ፓርቲ አገዛዝን ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መመለስ፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስከበርና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን መተግበር የግድ ይላል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.