Fana: At a Speed of Life!

በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የኢትዮጵያ ዝግጁነት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ90 ሺህ እስከ 100 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የሚገኝ ደን ይጨፈጨፍ ነበር። ይህ የደን ጭፍጨፋ ድርቅ፣ ጎርፍና የተለያዩ የተፈጥሮ ችግሮች እንዲከሰቱ ምክንያት ሲሆን ቆይቷል።
የመደመር መንግሥት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ድርቅ፣ ጎርፍ እና የተለያዩ የተፈጥሮ ችግሮችን ለመቀልበስ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ማከናወን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።
መርሐ ግብሩ ተግባራዊ በተደረገባቸው ባለፉት ዓመታት 48 ቢሊየን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ የተገኘው ውጤት የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጓል።
ባለፉት ዓመታት በተተገበረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ አድጓል። ይህንን ውጤት በማስቀጠል የደን ሽፋኑን ወደ 30 በመቶ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
የአረንጓዴ ዐሻራ የአፈር መሸርሸርን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ እንዲሁም ለም አፈር በውሃ እንዳይወሰድ ትልቅ ድርሻ መጫወት ጀምሯል።
በመርሐ ግብሩ በተሰሩ ስራዎች ከእርሻ ማሳ ላይ በየዓመቱ 130 ቶን ይሸረሸር የነበረው የአፈር መጠን በ50 በመቶ ዝቅ ብሏል።
አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ከማድረግ ባለፈ ደርቀው የነበሩ የውሃ አካላት መልሰው እንዲጎለብቱ እገዛ አድርጓል።
በጥቅሉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያን በጋራ ለማበልፀግና ሀገር ለመገንባት ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ቀጥሏል።
በዚህም መርሐ ግብሩ በስኬታማ መንገድ እየሄደ ሲሆን ዘንድሮም ተጠናክሮ ቀጥሎ 8 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል እየተሰራ ነው።
በመርሐ ግብሩ ከሚከናወኑ የችግኝ ተከላ ተግባራት መካከል አንዱ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ ንቅናቄ ሲሆን ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም 800 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።
የአረንጓዴ ዐሻራ በዓለማችን ላይ እያጋጠመ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሚሰራ ስራ መሆኑን የተገነዘቡት ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ዐሻራ እያሳረፉ ነው። ዘንድሮም የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።
‘ተስፋን እንትከል’ በሚል መሪ ሀሳብ በሚከናወነው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞች የመትከል መርሐ ግብር እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ድል ለማስመዝገብ ዝግጁ ሆነዋል።
ባለፈው ዓመት በነበረው የአንድ ጀምበር 700 ሚሊየን ችግኝ የመትከል ንቅናቄ ከዕቅዱ በላይ 714 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል። ዘንድሮም ከአራት ቀናት በኋላ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞች በመትከል ይህንን ድል ለመድገም ኢትዮጵያ ተዘጋጅታለች።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.