እግር ኳስን ለማቆም ጫፍ ደርሶ የነበረው ኮከብ – ራፊንሃ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የቢቢሲ ስፖርት አምደኛው ጊሌም ባላጌ፥ ብራዚላዊው ኮከብ “የእግር ኳስ ህልሜ አክትሞለታል” የሚል ውሳኔ ላይ የደረሰበትን አጋጣሚ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ይተርካል።
በብራዚሏ ፖርቶ አሌግሪ ከተማ የተወለደው ራፋኤል ዲያዝ ቤሎሊ (ራፊንሃ) እግር ኳስን የጀመረው እንደ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ለኳስ ባለው ፍቅር ብቻ አልነበረም።
ስኬታማ እግር ኳስ ተጫዋች መሆን፥ በከፋ ድህነት፣ በወንጀልና በአደንዛዥ ዕጽ ከሚታወቀው የትውልድ መንደሩ ማምለጫው ብቸኛ መንገድ መሆኑን ስለተረዳም ጭምር ነው።
የህልሙን መንገድ ተከትሎ ገና በልጅነቱ እግር ኳስን ቢጀምርም፤ የ18 ዓመት ወጣት እያለ ያጋጠመው የህይወት አጣብቂኝ ለዛሬ ስኬቱ መስፈንጠሪያ ሆኖታል።
የስፖርት አምደኛው እንደሚለው፥ በዚያ ወቅት ራፊንሃ ከሚጫወትበት የአቫይ ወጣት ቡድን ውጪ ሆኗል፤ ጉዳት አስተናግዷል፤ ፈላጊ ክለብ አጥቶ የእድል በሮች ሁሉ ተከርችመውበት ነበር።
እነዚህ ሁኔታዎች እግር ኳስ የማቆም አፋፍ ላይ አድርሰውት በነበረበት ወቅት፥ እናቱ የሰጡት ምክር ያበቃለት ለመሰለው ህልሙ ነፍስ ዘርቶለታል።
“የእግር ኳስ ጉዞህን ለማቆም ከወሰንክ፤ ቀሪውን እድሜህን አሁን ባለህበት ሁኔታ ለመኖር እንደወሰንክ እወቀው” ነበር ያሉት።
ጊሌም ባላግ በዚህ አምዱ፥ ከዚያች ቅጽበት በኋላ ራፊንሃ እስከ ባርሴሎና መልበሻ ቤት ያደረገው ጉዞ የጽናት፣ የዲሲፕሊን እና ራስን የማብቃት ታሪክ ነው ሲል ይገልጻል።
በእግር ኳስ ሕይወቱ ያሳየው ከፍታ የተሰጥኦ ብቻ ሳይሆን፤ የዓላማ ጽናት፣ የመስዋዕትነትና ለህልም የመኖር መሻት ውጤት መሆኑን ያነሳል።
ራፊንሃ እንደ አብዛኞቹ ብራዚላውያን ከዋክብት ብቃቱን በሀገሩ ብራዚል ሊጎች ለማሳየት አልታደለም፤ በዚህም ምክንያት ከአውሮፓ ዝቅተኛ ሊጎች መጀመር ግድ ብሎታል።
በፈረንጆቹ 2016 የፖርቹጋሉን ክለብ ቪቶሪያ ጊማሬሽ የወጣት ቡድን ከተቀላቀለ በኋላ ወደ ዋናው ቡድን ያደገ ሲሆን፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ሌላኛው የፖርቹጋል ክለብ ስፖርቲንግ አመራ።
በቀጣዩ ዓመት ወደ ፈረንሳዩ ሬን በማምራት ድንቅ ብቃቱን ያሳየ ሲሆን፤ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማቅናት ሊድስ ዩናይትድን መቀላቀል ችሏል።
የሊድስ ቆይታው በማርሴሎ ቤልሳ ስር ከኳስ ክህሎቱ ባሻገር ተክለሰውነቱን ያጠነከረበትና ቴክኒካዊ ብቃቱን ያጎለበተበት ነበር።
በሁለት ዓመት የኢላንድ ሮድ ቆይታው በፕሪሚየር ሊጉ በ29 ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ባሳየው አስደናቂ ብቃት በ50 ሚሊየን ፓውንድ መነሻ የዝውውር ሂሳብ ባርሴሎናን መቀላቀሉ አይዘነጋም።
በብሉ ግራናዎቹ ቤት በወቅቱ የክለቡ አሰልጣኝ በነበረው ዣቪ ስር፥ ራፊንሃ እንደ ስብስቡ አማራጭ የሚቆጠር እንጂ በቋሚነት የሚሰለፍ ተጫዋች አልነበረም።
በቋሚነት በሚጀምርባቸው ጨዋታዎችም በጊዜ ተቀይሮ የሚወጣ የነበረው ተጫዋቹ፤ በባርሴሎና ቤት በፍጥነት ለመድመቅ ተቸግሮ ነበር።
በፈረንጆቹ 2024 የካታላኑ ክለብ ከቀድሞ ተጫዋቹ ጋር ተለያይቶ ጀርመናዊውን አሰልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ ሲሾም ለራፊንሃ ሁኔታዎች ተቀየሩ።
በሀንሲ ፍሊክ ባርሴሎና ተከላካዮችን ለማለፍ የማይቸገር፣ በግብ ፊት ምህረት የለሽ ቁልፍ ተጫዋች መሆን ችሏል፤ በአሰልጣኙ የተሰጠው ሚና በራስ መተማመኑን ከፍ እንዳደረገለት ይነገራል።
በዚህ የውድድር ዓመት ብቻ በላሊጋው ለተከታታይ ሁለት ጊዜ ሀትሪክ መስራት የቻለው ብራዚላዊ የመስመር አጥቂ፥ በ12 ግቦች የላ ሊጋውን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ይገኛል።
በሀንሲ ፍሊክ ስር ለክለቡ ባደረጋቸው 98 ጨዋታዎች 69 ጊዜ ኳስና መረብን አገናኝቷል፤ 32 ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።
ከባርሴሎና ጋር ሦስት ጊዜ የላ ሊጋ ሻምፒዮን ሆኗል፤በ2024/25 የውድድር ዓመት የውድድሩ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በመሆን ተመርጧል።
ገና በ18 ዓመቱ እግር ኳስን ለማቆም ተቃርቦ የነበረው የባርሴሎና አምበል፤ በ2025ቱ የባሎንዶር ሽልማት ምርጥ 5 ውስጥ መካተት ችሎም ነበር።
በኃይለማርያም ተገኝ