አረንጓዴ ዐሻራ የአፍሪካን አህጉራዊ የአየር ንብረት ድርድር አቅም የሚገነባ ነው – ዲፕሎማቶች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአፍሪካን አህጉራዊ የአየር ንብረት ድርድር አቅም የሚገነባ ነው አሉ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች።
በአፍሪካ ኅብረት የመካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበር ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጃኩዌስ ዴማፎት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃና በከተማ ልማት ዘርፍ የገነባችው ልምድ አህጉራዊ ኩራትና ለሌሎች ሀገራትም ተግባራዊ አርአያ ነው።
እንደ ወዳጅነት ፓርክ ያሉ ተፈጥሮን ከዘመናዊ የከተማ ልማት ጋር ያጣመሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ኢትዮጵያ በከተሞች ውስጥ የአየር ንብረትን በብቃት መጠበቅ እንደምትችል ያረጋገጠችበት ማሳያ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ጥበቃ የሰጠችውን ከፍተኛ ትኩረት የሚያሳይ ነው ያሉት ዲፕሎማቱ፥ የውይይት አጀንዳዎችን ከአዳራሽ ወደ መሬት በማውረድ የተራቆቱ መሬቶችን በችግኝ መሸፈን ያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጋምቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ያንግ ላቦው በበኩላቸው፥ መርሐ ግብሩ የአፍሪካን አህጉራዊ የመደራደር አቅም በማሳደግ ከከፍተኛ የካርቦን ልቀቶች የሚገኘውን ፍትሃዊ ካሳ እንዲያገኙ ቁልፍ መነሻ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ያሳየችው ተግባራዊ ውጤት ሀገራቸው ተሞክሮውን ቀስማ ለመተግበር ዝግጁ እንድትሆን ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በሕዝብ ሰፊ ተሳትፎ መትከል የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የካርቦን ልቀትን ካሳ የመደራደር አቅምን አጎልብቷል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን አህጉራዊ የመሪነት ሚና እና የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮ በመውሰድ አብረው ሊሰሩ እንደሚገባም ዲፕሎማቶቹ አስገንዝበዋል።
በዮናስ ጌትነት