መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በዜጎችና በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በዜጎችና በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል አሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)
ኢትዮጵያና ማላዊ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትንና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፍልሰት እድሎችም ተግዳሮቶችም ያሉት ውስብስብ ሂደት ነው፡፡
ፍልሰትን በአግባቡ ማስተዳደር ከተቻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማፋጠንና ቀጣናዊ ውህደትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በአንጻሩ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በዜጎችና በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚመራውን ብሔራዊ ምክር ቤትን ጨምሮ በጠንካራ የፖሊሲ፣ የሕግ እና ተቋማዊ አደረጃጀቶች አማካኝነት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመዋጋት
ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለፍልሰት ምንጭ፣ መጓጓዣ እና መዳረሻ ሀገር እንዲሁም ማላዊ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚወስደው ደቡባዊ መንገድ ዋና ኮሪደርና ወሳኝ የመጓጓዣ መስመር መሆኗን አንስተዋል።
ማላዊ የፍልሰት ተጓጂዎችን በማስጠለል፣ ወደ ሀገር እንዲመለሱ በማድረግ እንዲሁም የተደራጁ ወንጀለኞችን ለፍትህ በማቅረብ ሂደት እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ ሀገራቱ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትንና በሰዎች የመነገድ ወንጀል የተሰማሩ አካላትን ለመዋጋት፣ ጤናማ የፍልሰት አስተዳደርን ለማስፈን፣ ዜጎችን ለመጠበቅና ተጎጂዎችን ለመደገፍ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያግዛል ብለዋል።
የማላዊ ሪፐብሊክ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ፒተር ሙኩሂቶ በበኩላቸው፤ ዜጎችን ለመታደግና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን ለማስቆም ማላዊ በቁርጠኛነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።