የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት እመርታዊ ጉዞ
የዓለም አቀፍ የውሃና የኃይል ገበያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታን ታሳቢ በማድረግም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን በማልማት ከሀገር ውስጥ የኃይል ፍላጎት ባሻገር ቀጣናዊ ትስስርን እያሰፋች ነው፡፡
የኢትዮጵያ የውሃ፣ የፀሐይ፣ የነፋስና የጂኦተርማል ብዝኅ የኃይል ፀጋዎች ልማት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን ማጎልበት የሚቻልበት ምኅዳር እየፈጠረ ይገኛል።
የታዳሽ ኃይል ልማት እመርታዊ ጉዞም የኤሌክትሪክ ማመንጨትን ከልማት፣ ከኢኮኖሚ ዕድገት፣ ኢኮኖሚ ዕድገትን ከቀጣናዊ ትስስር ጋር እያሰናሰለ የሚገኝ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ግብ ነው።
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር ዘላቂ ኢኮኖሚ እንድትገነባ አሰችሏል፡፡
የታዳሽ ኃይል ምንጮቹን በማቀናጀት የሚካሄደው ልማትም የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የከተማ ልማትና የዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን የኃይል መሠረተ ልማት እየገነባ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል የማመንጨት አቅሟን በማሳደግ የቀጣናው የኃይል ማዕከል እየሆነች ነው፡፡
የውሃ፣ የፀሐይ፣ የነፋስና የጂኦተርማል ሃብቶችን በማልማት የኤሌትክትሪክ የኃይል ምንጮችን፣ ደህንነትና ዘላቂነትን በማጎልበት የኢኮኖሚ መሰረት መፍጠር ተችሏል፡፡
በተለይም በዜጎች ትብብርና በሀገር አቅም የተገነባው የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ የኃይል ልማት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት እመርታዊ ጉዞ ኃይልን ከማመንጨት የተሻገረ ቀጣናዊ የጋራ ዕድገትና ብልጽግናን የማፋጠን አህጉራዊ የልማት ግብ ነው፡፡
የሕዳሴ ግድብ የኃይል አቅርቦት አቅም የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማሟላት ከማገዙ ባሻገር፣ ኃይልን ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር አዲስ ዕድል ፈጥሯል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በማልማት የራሷን የኃይል ደህንነት ከማረጋገጥ ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስርና ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ውህደት የሚያግዝ አዲስ ምዕራፍ እየገነባች ነው፡፡
ከጅቡቲ፣ ኬንያና ሌሎች ጎረቤቶች ጋር ያለውን የኃይል ትስስር በማስፋፋት የጋራ ዕድገትና ብልጽግናን የሚያጎለብቱ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያን ጨምሮ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብና የኃይል ትስስር መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
የኃይል ሽያጩም ኢትዮጵያን የኃይል ማዕከል በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ምንጭ በመሆን ጭምር ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር ተሰናስሎ ቀጥሏል፡፡