ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ልዩነቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ያስችላል – የመዲናዋ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ጉልህ ሚና አለው አሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች።
ከፋና ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉት የመዲናዋ ነዋሪዎች እንዳሉት÷ የሃሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተመካክሮ መፍታት ዘመኑን የዋጀና ቅቡልነት ያለው አካሄድ ነው።
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ባህሩ በየነ÷ ምክክሩ ሁሉን አቀፍና አካታች በመሆኑ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት ያስችላል ብለዋል።
በተለይም ለዘመናት የቆዩ ልዩነቶችን እልባት በመስጠት በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለው ሚና ጉልህ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ አቶ ዘመኑ አበበ በበኩላቸው÷ በመተሳሰብና በመከባበር እንዲሁም በጋራ በመነጋገር ያሉ ልዩነቶችን መፍታት እና መፍትሄ ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ የጋራ መግባባትን የሚያጠናክርና ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል ታሪካዊ ሒደት መሆኑን አውስተዋል፡፡
የምክክር ጉባዔው የሚስተዋሉ የሃሳብ ልዩነቶችና ፍላጎቶች ላይ በመመካከር ማህበረሰቡ ተግባብቶ የሚኖርበትን የተሻለ መፍትሄ ያመጣል ያሉት ደግሞ አቶ ዮናስ ተዘራ የተባሉት ነዋሪ ናቸው።
ምክክሩ የዘመናት ሀገራዊ ቅሬታና ስብራትን በሰለጠነ ምክክር በመጠገን ወደ መግባባት የሚያሻግር መድረክ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በትዕግስት ግዛቸው