Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎችን የማምረት አቅሟ እያደገ ነው – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅሟ እያደገ ነው አሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ።

13ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጤና አጠባበቅ ፌዴሬሽን ኮንፍረንስ እና ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን “በምሥራቅ አፍሪካ የማይበገር የጤና ኢኮኖሚ መገንባት” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በዚሁ ወቅት ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለመድኃኒት ቅመማ፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለምግብ ዋስትና ትልቅ ሚና እየተወጣ ነው፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ጠንካራ የጤና ተቋማትን መገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በአፍሪካ እንደ ኢቦላ ዓይነት ወረርሽኝ፣ የጤና ደህንነት፣ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ውስንነት የጋራ ስጋት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለዚህ ችግር አፍሪካውያን በጋራ መስራት አለብን ያሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በጤና አጠባበቅ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቷን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁን ማህበረሰብ አቀፍ የጤና ተቋም መገንባቷን ገልጸው፤ በጤና ቴክኖሎጂ፣ በሰው ሀብት ልማትና በመሰረታዊ የጤና መለኪያዎች ላይ መሻሻል ታይቷል ነው ያሉት፡፡

የዲጂታል ጤና ሥርዓት ምርጫ ሳይሆን፤ አፍሪካውያን ብሔራዊ የጤና አጀንዳቸው ሊያደርጉት የሚገባ ሥርዓት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት ደረጃ ሦስት ማግኘቷን አንስተው፤ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያዎችን ማምረት ቁልፍ አጀንዳዋ ነው ብለዋል።

ለአፍሪካ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት የግሉ ዘርፍ ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የተመቸ ሥነ ምህዳር መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.