የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ታሪካዊ ድልን በጋራ ጽፏል – አቶ መሀመድ እድሪስ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሰላም አብሮነት ምሳሌ የሆነ ተቋም ነው አሉ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፡፡
የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ 15ኛ ዓመት ምስረታ በዓል እና 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ሚኒስትሩ እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባለፉት 15 ዓመታት አብሮነትን ለማጠናከር እና ሰላምን ለማጽናት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
ተቋሙ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነት፣ አጋርነት እና ወዳጅነት ለማጠናከር የተደረገውን ጥረት በመደገፍና ውጤታማ በማድረግ ረገድ አወንታዊ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡
ጉባኤው ላለፉት 15 ዓመታት ችግሮችን በጋራ በማለፍ ለአብሮነት እና ለሰላም ምሳሌ ሆኗል ያሉት ሚኒስትሩ÷ በዚህም ተቋሙ ትልቅ የድል ታሪክ መጻፉን ገልጸዋል፡፡
ከሰላም እና አንድነት ተልዕኮዎቹ በተጨማሪ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳዎችን በማስረከብ አስተዋፅኦ ማድረጉን ጠቁመው÷ ይህም ተቋሙ ለሀገር እና ለህዝብ ያለውን አለኝታነት ያሳይል ብለዋል።
ከልዩነት ይልቅ በጋራ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ማተኮር ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ÷ ተቋሙ ከሁሉም በላይ ለሰላም፣ ለእውነት እና ለፍትህ ምሳሌ የሆነ ማንነት በመገንባት ህዝቡን ሊመራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ የተቋሙን የ15 ዓመታት ጉዞ በመፈተሽ ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ በማስቀጠል እንዲሁም የታዩ ከፍተቶችን በማረም የተቋሙን ተልዕኮ የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ