Fana: At a Speed of Life!

የአከራይና ተከራይ ውል እድሳት ማጠናቀቂያ የጊዜ ገደብ እስከ ጳጉሜን 5 ቀን ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአከራይና ተከራይ ውል እድሳት ማጠናቀቂያ የጊዜ ገደብ እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2018 ዓ.ም ተራዝሟል አለ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ፡፡

ቢሮው እንዳስታወቀው÷ ከሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው የአከራይና ተከራይ ውል ምዝገባና እድሳት አገልግሎት እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ ጊዜ ገደብ ተቀምጦ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን በጊዜው አሟልተው ያልቀረቡ፤ በተሰጠው የጊዜ ገደብ በልዩ ልዩ ምክንያት ከአዲስ አበባና ከሀገር ውጭ የነበሩ ተዋዋዮች መኖራቸውን ቢሮው መገንዘቡን ነው የገለጸው፡፡

በህብረተሰቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ መሰረት የመጨረሻ ተጨማሪ እድል መስጠት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ያስታወቀው ቢሮው÷ በዚህም የአከራይና ተከራይ ውል እድሳት ማጠናቀቂያ የጊዜ ገደብ እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በመሆኑም እስከ ዛሬ ውላቸውን ያላደሱ ሁሉም አከራዮችና ተከራዮች ይህንን የመጨረሻ እድል በመጠቀም በክፍለ ከተሞች፣ በሁሉም የመሶብ አንድ ማዕከላት እና ለዚሁ አገልግሎት በተዘጋጁ ቦታዎች በመቅረብ ውላቸውን እንዲያድሱ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.