የልጅነታችን በመስከረም
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር የዛሬ ብቻ ሳትሆን የትናንት የጋራ ትዝታ ውጤት ናት። በዜጎች ልብ ውስጥ የተጻፈ፣ የሚታወስና የሚናፈቅ ትናንት፣ በጋራ ሀገር ግንባታ ውስጥ ወሳኝ ግብዓት ነው።
አንድ ህዝብ የጋራ ትዝታ ሲኖረው፣ ከቋንቋ፣ ከሃይማኖት ወይም ከጂኦግራፊያዊ አካባቢ ልዩነት በላይ የሚያስተሳስረው የልብ ትስስር ይፈጠራል። ምክንያቱም የልጅነት ትዝታ ማንነትን ከፖለቲካ በላይ የሚያገናኝ፣ በስሜት ላይ የተመሠረተ ትስስር ስለሆነ ነው።
መስከረም አዲስ ነው፤ ልጅነታችንን ከሚያስናፍቁን ወቅቶች ሁሉ ቀዳሚ። መስከረም የአዲስ ቀን መምጣት፣ የአዲስ ወር መጥባት ምልክት ነው።
ለአዲስ ዓመት አዲስ ልብስ ተገዝቶልን እስክንለብሰው ድረስ የነበረን ጉጉት፣ ትምህርት ቤት ተከፍቶ ጓደኞቻችንን እስክናገኝ ያለን ናፍቆት፣ አዲስ ደብተር፣ አዲስ ክፍል፣ አዲስ መንፈስ… አዲስነት የሚታወጅበት ወር ነው መስከረም።
እስኪ ዛሬ ልጅነታችንን በትዝታ እንጋራ። በጋራ ያለፍንበትን፣ በህብረት የተሻገርነውን ያን ዘመን አብረን እንተዝተው…
መስከረም ሲመጣ የአስኳላ በሮች ይከፈታሉ። የትምህርት ቤቶቻችን ሜዳዎች በክረምት ዝናብ ለምልመው ሳር ሞልቷቸዋል፤ ያደገ፣ ልምላሜ የተላበሰ ሳር ይሆናሉ።
ያንን ሳር አጠላልፈን የምንቋጥረው፣ ተጠልፎ የሚወድቀውን ጓደኛችንን እያየን የምንስቀው ሳቅ ትዝ አላችሁ? ያቺ ስትስቅ ዓይኗ የምትጨፍነው ጓደኛችን የት ይሆን ያለችው?
ደወል ሲደወል ተሰልፈን ወደ ክፍል የምንገባበት ስርዓት፣ በአዲስ መምህር ስም ስንጠራ የልብ ትርታችን የሚጨምርበት ቅጽበት፣ አዲስ ጓደኛ ለማፍራት ያለን ስስት… እነዚህ ሁሉ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ተቀርጸው የቀሩ ህያው ትዝታዎቻችን ናቸው።
መስከረም ሜዳውን በአደይ አበባና በቄጤማ ይሞላዋል። ከሳሩና ከአደይ አበባው ቀጥፈን ደብተራችንን የምናስውበው፣ በቢጫና በአረንጓዴ ቀለም ደብተራችንን የምናሸበርቅበት ትዝታ አልረሳችሁትም አይደል?
ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው እየዞርን «እንቁጣጣሽ» እያልን አደይ አበባ የምናበረክትበት፣ በምላሹ ገንዘብም ይሁን ጣፋጭ ነገር የምንቀበልበት ልማድ፣ «አበባየሆሽ» የሚለውን ዘፈን መንደር ለመንደር እየዞርን የምንዘፍንበት ማለዳ፣ ያ ሁሉ ትዝታ ዛሬም በልባችን ውስጥ ትኩስ ሆኖ ይኖራል።
አዲስ ዓመት ሲመጣ ቤታችን በዶሮ ወጥ ጠረን ይሞላል፤ እናቶቻችን ገና በሌሊቱ ተነስተው ሲያበስሉ የሚወጣው ጭስና መዓዛ ከእንቅልፋችን የሚቀሰቅሰን ደውል ነበር።
አዲስ ልብስ ለብሰን፣ በደስታ ተውበን ከቤተሰብ ጋር የምንነሳበት ጠዋት፣ አያቶቻችንን እጅ የምንነሳበት፣ በረከት የምናገኝበት ስርዓት፣ ጎረቤት ለጎረቤት እየተጠራሩ በጋራ የምንቀርብበት ማዕድ… እነዚህ ሁሉ የመስከረም ትዝታዎቻችን ናቸው።
ልጆች በአዲስ ልብሳችን ቄንጥ ተሞልተው ወደ ጎረቤት ቤት ስንሮጥ፣ «እንኳን አደረሳችሁ» የሚለው የሰላምታ ቃል ከሁሉም አፍ ሲደመጥ፣ መላው ሰፈር በአንድ የደስታ ስሜት ተውጦ የአዲስ አመት አዋጅ ይሆናል።
በመስከረም ዋናተኛ የምንሆነውስ ትዝ አላችሁ? ከትምህርት ቤት መልስ ሰፈራችን ያለ ወንዝ እንወርድና እንዋኛለን። ዋኝተን ስንጨርስ ለምን ነበር ነጭ አመዳሞች የምንሆነው? አመዳምነታችንን ለማጥፋት የምናደርገው ትግልስ?
ወራጅ ውሃ ውስጥ ተንቦራጭቀን ልብሳችን እየረጠበ ወላጆቻችን ቢያውቁብን በሚል ፍርሃት፣ ልብሳችንን በፀሐይ አድርቀን ወደ ቤት ስንገባ ንፁህ መስለን ለመታየት ያደረግነው ጥረት፣ ውሎ አድሮ ግን ተደርሶበት የምንቆነጠጠው ቁንጥጫ!
ሁሉም ስናስበው ፈገግ የሚያሰኘን ትዝታ ነው። ወንዝ ዳር ኳስ የምንጫወትበት፣ የጭቃ ሸርተቴያችን፣ ትንንሽ ጀልባ ከወረቀት ሰርተን በውሃ ላይ የምናንሳፍፍበት ልጅነት፣ የብዙዎቻችን ትዝታ ነው።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመስከረምን ጠረን ሲያሸት የአደይ አበባን ቀለም ሲያይ፣ ተመሳሳይ የልጅነት ናፍቆት ውስጡ ይላወሳል።
ይህ የጋራ ስሜት ነው ብሔራዊ ማንነትን ከመሬትና ከድንበር በላይ አጥብቆ የሚያስተሳስረው።
በአፈወርቅ እያዩ