ጳጉሜን 2 ‘የማንሰራራት ቀን’ በተለያዩ ክልሎች እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጳጉሜን 2 ‘የማንሰራራት ቀን’ በአፋር፣ ጋምቤላ እና ሲዳማ ክልሎች እየተከበረ ይገኛል።
በአፋር ክልል ዕለቱን አስመልክቶ በሠመራ ከተማ ‘ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሰራራት’ በሚል መሪ ኃሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ሲከበር የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የሠመራ ኢንዱስትሪያል ፓርክና የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ዑመር ኑር አርባ፤ ክልሉ ከነበረበት የልማት ሁኔታ አንፃር በለውጡ መንግስት በተሰራው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች የኢኮኖሚ ማንሰራራት ማሳየቱን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ጳጉሜን 2 ‘የማንሰራራት ቀን’ በጋምቤላ ክልል የተከበረ ሲሆን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር)፤ ከሀገራዊ የለውጥ እምርታዎች በኋላ ሀገሪቱ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስህተቶቿን በማረም ወደ ቀደመ ገናናነቷና ማንሰራራቷ እየተመለሰች ትገኛለች ብለዋል።
በቀጣይም የታለሙ የልማት ግቦችን ለማሳካትና ዘላቂ ብልፅግናን ለማረጋገጥ መላው የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመቆም የተጀመሩ ታላላቅ የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካት በግንባር ቀደምትነት የመደገፍ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ማንሰራራት በሚል መሪ ኃሳብ የሚከበረው ጳጉሜን 2 ቀን በሲዳማ ክልልም ከማለዳ ጀምሮ በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች የተሰሩ የልማት ስራዎች በመጎብኘት እና በፓናል ውይይት እየተከበረ ይገኛል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የሲዳማ ክልል እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ መምሩ ሞኬ እንዳሉት፤ በግብርናው ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ የታየው እመርታ ተስፋ ሰጪ ነው።
ከግብርና ዘርፍ በተጨማሪ በኢንዱስትሪ፣ በመሰረተ ልማት፣ በማዕድን እና በገቢ ዘርፍ ባለፉት አመታት የተሰሩ ስራዎች የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል።