የሌማት ትሩፋት፡ የግብርናው ዘርፍ አዲሱ አስደናቂ የስኬት ገጽ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የበርካታ ተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ሀገር ነት፤ በተለይም በእንስሳትና እፅዋት ሃብቶቿ በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከግንባር ቀደምቶቹ ትሰለፋለች፡፡
ነገር ግን በተፈጥሮ የታደለችውን ጸጋ ያክል ከእነዚህ እምቅ ብቶቿ መጠቀም ሳትችል ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡
የእንስሳትና የእጽዋት ሃብቶች በቤተሰብ ደረጃ ውጤትን በሚያስገኝ መልኩ ማምረትም እምብዛም የተለመደ አልነበረም፡፡ በዚህም ሕብረተሰቡ ከእነዚህ ሃብቶች የሚገኘውን ጥቅም በአቅሙ ያክል ተቋዳሽ እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡
በእንስሳት ሃብት በበቂ ሁኔታ አምርቶ አለመጠቀም፤ ወደ ገበያ አውጥቶ ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በላይ የሰው ልጅ ጤነኛ ሆኖ ለመኖር የሚያስፈልጉትን ከምግብ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች በተፈለገው ልክ እንዳያገኝ ያደርጉታል፡፡
የመደመር መንግሥት እሳቤ የሆነው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር መተግበር ከጀመረ አንስቶ ግን በእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ላይ ከፍተኛ እመርታ ተመዝግቧል፡፡
የሌማት ትሩፋት ወተት፣ እንቁላል፣ አሳ ማርና ስጋን በየዕለት ማዕድ ውስጥ የሚካተቱ እንዲሆኑ በማድረግ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን እንድታረጋግጥ የሚያስችል ሀገራዊ ትልም ነው፡፡
በዚህም እነዚህን ምርቶች በቤተሰብ ብሎም በመንደር ደረጃ በሰፊው እንዲመረቱ መርሐ ግብሩ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሩ ጅማሮውን ካደረገ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ መሰረታዊ የሆኑት የእንስሳትና የእጽዋት ምርቶች እድገትን አስመዝግበዋል፡፡
የወተት ምርት አቅርቦትን ስንመለከት፤ መርሐ ግብሩ ጅማሮውን ሲያደርግ በዓመት 7 ነጥብ 1 ቢሊየን ሊትር የነበረ ሲሆን ÷ አሁን ላይ ወደ 15 ነጥብ 2 ቢሊየን ሊትር አድጓል፡፡
የዓሳ ምርትን በሚመለከት ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው 78 ሺህ ቶን ወደ 307 ሺህ ቶን ማደግ ችሏል፡፡
በዶሮ እርባታ 26 ሚሊየን የነበረው የጫጩት ሥርጭት ወደ 184 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን÷ በተመሳሳይ በማር ምርት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 428 ሺህ ቶን የማር ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የሌማት ትሩፋት በቤተሰብ ደረጃ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን በዕለት ከዕለት የምግብ ተዋጽኦዎች ውስጥ የማካተት ልምምድን እጅጉን የጨመረ ሲሆን÷ ሥርዓተ ምግብን በማሻሻል ጤናው የተጠበቀ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡
ለአርሶ አደሩ ብሎም በከተማ ግብርና ላይ ለተሰማሩ ዜጎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመፍጠር የኢኮኖሚ አቅምን እያሳደገ መጥቷል፡፡
የሌማት ትሩፋት ኢትዮጵያ ለእንስሳትም ሆነ ለእጽዋት ምርት አመቺ የሆነ የተፈጥሮ ጸጋን የታደለች ሀገር በመሆኗ ይህንን ፀጋ ተጠቅሞ ጤናው የተጠበቀ፣ የምግብ ዋስትናው የተረጋገጠና በኢኮኖሚ ጠንካራ ማሕበረሰብ ለመገንባት የተወጠነ የግብርናው ዘርፍ የስኬት ማሳያ መርሐ ግብር ነው፡፡
በመልካም ፈቃዱ