የጤና ሚኒስቴር የኅብር ቀንን አስመልክቶ ነጻ የሕክምና እና የምርመራ አገልግሎት ሰጠ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት እየተከበረ የሚገኘውን የኅብር ቀንን አስመልክቶ ነጻ የሕክምና እና የምርመራ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ጳጉሜ 4 የኅብር ቀንን ስናከብር ህብረብሄራዊ አንድነታችንን በማስጠበቅ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለማሻገር ሁላችንም በጋራ ልንቆም ይገባል፡፡
በመስቀል አደባባይ በተደረገው የነጻ ምርመራ እና ሕክምና አገልግሎት 30 የግል እና 15 የመንግሥት የጤና ተቋማት ተሳታፊ ሆነዋል።
በመርሐ ግብሩ የአይን፣ የጆሮ፣ የአንጀት፣ የቆዳ፣ የውስጥ ደዌ፣ የቀዶ ሕክምና፣ የማህፀን፣ የካንሰር፣ የላቦራቶሪ እና የዲያግኖስቲክስ ነጻ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።
የኅብር ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአዲስ አበባ ብቻ በአንድ ቀን ለ10 ሺህ በላይ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጥ ይሰጣል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም በሃገር አቀፍ ደረጃ በ12 ክልሎች እና 2 ከተማ መስተዳደሮች ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ነጻ የምርመራ እና ህክምና አገልግሎት እንደሚያገኙ ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡