ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ባበረከቱልን ስጦታ ተደስተናል -የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባበረከቱልን ለአዲስ ዓመት በዓል መዋያና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደስተናል አሉ ስጦታውን የተረከቡ የህብረተሰብ ክፍሎች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) መጪውን የ2019 ዓ.ም የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በዓልን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች የበዓል ስጦታ እንዲሁም በጽሕፈት ቤቱ ድጋፍ ለሚያድጉ ሕፃናት የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ አበርክተዋል።
ስጦታ ከተበረከተላቸው መካከል አቶ አዲስ ሳህሌ ÷ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያበረከቱላቸው ስጦታ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያደርጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ለልጆቻቸው የተበረከተላቸው የትምህርት መርጃ ቁሳቁስም በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ያለምንም ችግር ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልፀው ፤ለድጋፉ ምስጋና አቅርበዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወ/ሮ ሞቱ ቶለሳ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓላት ወቅት የሚያደርጉት ድጋፍ የመረዳዳትና የእርስ በእርስ መተሳሰብ ባህልን እያጎለበተ መሆኑን አስረድተዋል።
የተደረገላቸው ስጦታ በዓሉን በደስታ በማሳለፍ ልጆቻቸው ሙሉ ተስፋና ዝግጅት ሰንቀው ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ የሚያስችላቸው መሆኑንም አብራርተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድጋፍ ከሚያድጉ ተማሪዎች መካከል ተማሪ እቴነሽ ዓለሙ በበኩሏ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስጦታ በዓሉን ከቤተሰቧ ጋር በታላቅ ደስታ እንድታሳልፍ እና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ እንድታገኝ ዕድል የፈጠረላት መሆኑን ገልጻለች።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጊዜው ለሚያደርጉላቸው የበዓል መዋያና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ልባዊ ምስጋናዋን አቅርባለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሁል ጊዜም ለበዓል መዋያ ለሚያደርጉላቸው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወ/ሮ ትናኝ አየነው ናቸው።
ሌላኛዋ ስጦታ ከተበረከተላቸው መካከል ወ/ሮ እመቤት ሶሪ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያበረከቱላቸው ድጋፍ ልጃቸው በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ትምህርቱን ያለ አንዳች ችግርና ስጋት የሚከታተልበትን ምቹ ዕድል የፈጠረለት መሆኑን ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።