Fana: At a Speed of Life!

የዲጂታል ሕዳሴ – ለዘመናዊ ኑሮ እና ኢኮኖሚ ግንባታ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራት ራሳቸውን ለማብቃት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ አገልግሎትን በጥራትና በቅልጥፍና ማድረስ፣ ዜጎችን በቴክኖሎጂ እውቀት ማብቃት ላይ መስራት በጠቅላላው ኢኮኖሚውን በዲጂታል ዘርፍ መደገፍ የሚጠበቅ ነው፡፡
የዲጂታል 2025 ትግበራን አጠናቅቃ ዲጂታል 2030ን እያሳካች የምትገኘው ሀገራችን የወጣቶችን የፈጠራ ክህሎት ለማሳደግ የሚያስችለው የ5 ሚሊየን ኮደርስ ንቅናቄን አሳክታ፤ አሁን ቁጥሩን በማሳደግ 7 ሚሊየን ኮደርስ ለማፍራት እየሰራች ትገኛለች።
በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ የሆነው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ መገንባትም ሌላው ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ እየተገበረች የምትገኘው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መንገድ የወረቀት አሰራርን የቀነሰ፤ የተወሳሰበ የቢሮክራሲ ስርዓትንና የሙስና ተጋላጭነትን በማስቀረት የሕዘብን እርካታ ያረጋገጠ ነው፡፡
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት መጀመር የዜጎችን ሙሉ መረጃ በማዕከላዊ ስርዓት ለመያዝና ለማስተዳደርና እንዲሁም ዜጎች የትኛውንም አገልግሎት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያቸውን ብቻ ተጠቅመው ማግኘት እንዲችሉ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
በተጨማሪም የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ አገልግሎቶችን በማቀናጀት፤ በአንድ ቦታ እንዲገኙ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ ወደ ተግባር አምጥቷል፡፡
ይህም ጊዜያቸውን፣ አቅማቸውን እንዲሁም ገንዘባቸውን የሚቆጥቡበትን መንገድ የቀየሰና በወረቀት ይሰሩ የነበሩ ስራዎችን በማስቀረት ገንዘብና ጊዜን የሚቆጥብ ሆኗል፡፡
እንደ ሳፋሪኮም ያሉ ኩባንያዎች በቴሌኮም ዘርፉ እንዲቀላቀሉ መደረጉ የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል የውድድር አውድ የፈጠረ ሲሆን፤ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ እድል ፈጥሯል፡፡
እንደ ቴሌ ብር፣ ኤም ፔሳ እንዲሁም የተለያዩ የዲጂታል የክፍያ አማራጮች ወደ ተግባር የመጡበት የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት ተገልጋዮችና ሸማቾች ሳይጉላሉ የደህንነት ስጋትን ባስቀረ መንገድ ክፍያ እንዲፈጽሙ አስችሏል፡፡
እነዚህ ማሳያዎች በዲጂታል ዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችን እንዲሁም ዛሬ የደረስንበትን የከፍታ መልክ ማሳያ ብቻ ሳይሆኑ፤ ኢትዮጵያ ነገ የምትደርስበትን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡
በቤተልሔም ግርማ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.