የብሔራዊ ፋይዳ መታወቂያ ምርጥ ተሞክሮ ለአፍሪካ ሀገራት
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሔራዊ የፋይዳ መታወቂያ ከኢትዮጵያ ባሻገር በዛምቢያ፣ ሞዛምቢክ እና ቡሩንዲ የሙከራ ትግበራ ሊጀምር ነው አሉ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው የነገ ቀንን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የፋይዳ መታወቂያ “አንድ ሰው አንድ ነው”በሚል መርህ የዲጂታል ማንነትን የመመዝገብና የማረጋገጥ ሥራን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝጋቢዎች ቁጥር 50 ሚሊየን መድረሱን ጠቁመው ÷ ይህም ወንጀልን ለመከላከል፣ አገልግሎቶችን በዲጂታል በማስተሳሰር ለማሳለጥና በግለሰቦች፣ በተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መካከል አስተማማኝ ትስስርን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ፋይዳን ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተሠርቶ እስካሁን 150 የመንግሥት፣ የግል፣ የስታርታፕ እና ሌሎች ተቋማት በፋይዳ ትስስር ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በፋይዳ መታወቂያ አገልግሎት ከ200 ሚሊየን በላይ ማንነትን የማረጋገጥ ተግባራት መከናወናቸውን ነው የገለጹት፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የምዝገባ ማዕከላትን ለማስፋፋት በተከናወነ ሥራ የጣቢያዎቹ ቁጥር ወደ 12 ሺህ ገደማ መድረሳቸውን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፥ በዚህም እስካሁን 50 ሚሊየን ሰዎች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ወደ ሰፊ የዲጂታል መሠረተ ልማት ማዕከል በማደጉ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር በልማት ድርጅትነት መቋቋሙን አስታውሰዋል።
ይህም በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ተሞክሮዎች እንዲቀስሙና በትብብር ለመሥራት ከፍላጎት ያለፈ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ፍላጎት ካሳዩ ሀገራት መካከል የተወሰኑት የመግባቢያ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን ገልፀው÷ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ቴክኖሎጂን በሙከራ ደረጃ በዛምቢያ፣ ሞዛምቢክ እና ቡሩንዲ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።
ይህ እንቅስቃሴ ተቋሙ አፍሪካውያን በራሳቸው አቅምና እርስ በርስ በመደጋገፍ የዲጂታል ሽግግርን ማሳካት እንደሚችሉ የሚያሳይና የደቡብ ለደቡብ ትብብርን ለማጠናከር ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል።