Fana: At a Speed of Life!

የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስራችን ትልቅ ድል ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ የመጀመሪያ ምዕራፍ ፕሮጀክትን በዛሬው ዕለት መርቀው ከፍተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሉት፤ የማዕከሉ ማስፋፊያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው፡፡

የኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ጉዞ በተግባር የታነጸበት ሥራ መሆኑን ገልጸው፤ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬት ትልቅ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት፡፡

በ60 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፍያ የመጀመሪያ ምዕራፍ ፕሮጀክት በዓመት እስከ 1 ሚሊየን ባለ 20 ጫማ ኮንቴነሮች የማስተናገድ አቅም ያላቸው ጣቢያዎችና ዘመናዊ መጋዘኖችን የያዘ ነው፡፡

የደረቅ ብትን ጭነቶችን በሀገር ውስጥ እንድናሽግ ማስቻሉ የውጭ ምንዛሪን ከመቆጠብ ባለፈ ለዜጎቻችን ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የማዕከሉን የአሰራር ፍጥነት ለማሳደግ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተተከለው የባቡር ላይ ክሬን ከባቡር መስመር የሚደረገውን የኮንቴነር ዝውውር በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚያከናውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሙሉ አሰራሩ በዘመናዊ ዲጂታል መሰረተ ልማት የተሳሰረ በመሆኑ ለተገልጋዮች ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎትን ያሳልጣል ነው ያሉት።

ይህ ማዕከል ከኢትዮ-ጅቡቲ መስመር ባሻገር ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳንን እና ዩጋንዳን የሚያስተሳስረው የ‘ደሱ’ ኮሪደር አካል መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ይህም ሀገራችን በዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ደረጃ ላይ ያላትን ስፍራ የሚያሻሽልና የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስራችንን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግር ትልቅ ድል ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.