አዲስ ዓመት እና እቅድ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ ተስፋ ይሰነቃል፤ ሰዎች ለአዳዲስ ፈተናና እድሎች ራሳቸውን ያዘጋጃሉ፡፡
የአዲሱን ዓመት መምጣት አስታክከው ለቀጣይ የህይወታቸው ጉዞ አዳዲስ ውሳኔዎችን ይወስናሉ፡፡
በአዲሱ ዓመት የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው በመመኘት፤ የትናንቱን ስኬትና ውድቀት መርምረው፤ መንፈሳቸውን አድሰው ይቀበላሉ፡፡
ያለፈውን ዓመት የህይወት ጉዞ ገምግሞ አዲስ እቅድ የማውጣት ልምምድ ውጤታማ ያደርጋል፡፡ የዘመን ለውጥ በሰዎች ላይ ተስፋን ይፈጥራል እንዲሁም ለለውጥ ያነቃቃል፡፡
በኢትዮጵያ በአዲስ ዓመት የሚታዩት የተፈጥሮ ክስተቶች ሁሉ የሰውን ልጅ ተስፋ የሚያለመልሙ ናቸው፡፡
የዝናቡ መገታት፤ የጸሐይዋ መገለጥና የምድሪቱ መፍካት የአዲስ ጅማሮ አመላካች በመሆቸው ለአዲስ የለውጥ ውሳኔ አነቃቂ ናቸው፡፡
እያንዳንዱ ቀን ለአዲስ ጅማሮ እድል የሚሰጥ ሲሆን፤ አዲስ ዓመት ደግሞ ሰዎች ያለፈውን ዓመት የህይወት መንገድ ገምግመው የተሻለ ማንነት ለመገንባት የሚዘጋጁበት ነው፡፡
በዚህም ያለፈውን ዓመት ጉዞ ቆም ብሎ በመቃኘት በትምህርት፣ በስራ፣ በትዳር አልያም በሌሎች የህይወት መንገዶች የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት ከራስ ጋር በመማከር በአዲስ ዓመት አዲስ ነገር ማቀድ የተሻለ ውጤታማ ያደርጋል፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!