Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ አንድነት ኃይል ነው – ታይም አፍሪካ መፅሔት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጄክት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አንድነት ኃይል ነው አለ የታይም አፍሪካ መፅሔት፡፡

መፅሔቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልከቶ ባወጣው ሀተታ÷ ግድቡ በዘመናችን ካሉ ታላላቅ የአፍሪካ ታሪኮች አንዱ እና የአፍሪካውያን የጋራ ሀብት መሆኑን ጠቅሷል፡፡

በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ይህ ፕሮጄክት በአፍሪካ ትልቁ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መሆኑን እንዲሁም አፍሪካ ከገነባቻቸው ታላላቅ የመሰረተ ልማት ፕሮጄክቶች አንዱ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ግድቡ 5 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው በመግለፅ ይህም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ተግዳሮት የሆነውን የኃይል አቅርቦት ችግር በመፍታት ለንግድ ሥራዎች፣ ለማኑፋክቸሪንግ እና ለኢንዱስትሪ ዘርፎች በቂ ኃይል ለማቅረብ ያግዛል ብሏል፡፡

የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቡ የኢትዮጵያን የኃይል ዘርፍ እየለወጠ እና የኢንዱስትሪ ልማትን እየደገፈ እንደሚገኝ በመጠቆም ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በኃይል አቅርቦት እያስተሳሰረ ይገኛልም ነው ያለው፡፡

በዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጄክት ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያን በመሰረተ ልማት ዘርፍ እንዲተሳሰሩ ያደረገ የአፍሪካ አንድነት ኃይል መሆኑን አስረድቷል፡፡

የአፍሪካውያን ግዙፍ ፕሮጄክቶች ቀደም ሲል በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ወይም ኢንቨስተሮች ብድር ይገነቡ እንደነበር በማስታወስ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግን ይህን ታሪክ በመቀየር በራስ አቅም መገንባቱን ገልጿል፡፡

በዚህም ግድቡ አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም ታላላቅ ፕሮጄክቶችን መገንባት እንደሚችሉ እንዲሁም አፍሪካውያን በውጭ የፖለቲካ ተፅዕኖ ሳይገቱ የተፈጥሮ ሀብታቸውን ማልማት እንደሚችሉ ያሳዩበት መሆኑን ነው መጽሔቱ ያብራራው፡፡

ግድቡ ከሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብነት ባለፈ ትልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነ እና ታላቁ በአፍሪካ ቀንድና በአባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ያለውን የጂኦ ፖለቲካ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ የቀየረ ሜጋ ፕሮጀክት ነው ብሏል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.