ባሕር በር፤ ብሔራዊ ደኅንነትና ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ውሃ የሰው ልጅ የመኖር መሠረት ነው፤ ከዚህም ባሻገር በሀገራት እድገትና ስልጣኔ መመስረት እንዲሁም ሉዓላዊነት መከበር ውስጥ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡
የጥንት ስልጣኔ ባለቤቷ ምድረ ቀደምት ኢትዮጵያ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ከነበረው የአዱሊስ ወደብ ጀምሮ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ታካሂድ ነበር፡፡
ከ130 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የወጪ ገቢ ንግድ የምታካሂደው ጅቡቲ ወደብን ተጠቅማ በመሆኑ፤ ይህ ችግር በቀጥታ ተጽዕኖ ያሳድርባታል፡፡
የዓለም አቀፍ ህግ ወደብ አልባ የሆኑ ሀገራት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ወደብ ባላቸው ሀገራት በኩል እንዲያሳልፉ መብት ይሰጣል፤ ነገር ግን ይህ የሚሆነው በወደቡ ላይ ሉዓላዊ መብት ያላቸው ሀገራት ለሚያስቀምጡት ህግ መገዛትንና በቅድመ ሁኔታቸው መስማማትን ይፈልጋል፡፡
ይህም ደህንነቷን አደጋ ላይ እንዲወድቅ የሚያደርገው በመሆኑ፤ በዋናነት ብሔራዊ ደህንነትና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅም የባሕር በር ወሳኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡
ዓለም አቀፍ የደህንነት ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለዋወጡና ለመተንበይ አስቸጋሪ እየሆኑ መጥተዋል፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ ላይ የተፈጠሩ ቀውሶች ወደ ቀይ ባሕር መስፋፋት የነዳጅና የሸቀጦች አቅርቦት ላይ ከሚያመጣው ተጽዕኖ ባሻገር ለከፍተኛ የደኅንነት ስጋትም የዳረገ ሆኗል፡፡
በሀገር ደህንነት ላይ ስጋት የሚደቅኑ በባሕር ላይ የሚፈጸሙ ህገወጥ ዝውውሮችን፣ የአሸባሪ ቡድን እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የሚያስችል ጠንካራ የባሕር ኃይል ስራን ይፈልጋል፡፡
በባሕር ላይ የሚመጡ የደኅንነት ስጋቶችን መሬት ላይ ሆኖ ለመመከት አስቸጋሪ በመሆኑ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን አስታከው ለሚመጡባት የደኅንነት ስጋቶችን መመከት የምትችለው የባለቤትነት መብቷን አስከብራ መቆም ስትችል ነው፡፡
ጠንካራ የባሕር ኃይልን የነበራት ኢትዮጵያ የጦር መርከቦቿ ቀይ ባሕርን እያሰሱ እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ይደርሱ እንደነበር ይነሳል፡፡
ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ጦቢያ መጽሔት ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ እንዲህ ይላሉ፤ “ኢትዮጵያ በታሪኳ ያለፈቻቸው መነሳትና መውደቅ ከባሕር ጋር ከነበራት ቅርበትና ርቀት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለው፡፡
የባሕር በር በእጇ በነበረበት ዘመን የጎለበተችና የበለጸገች ኢትዮጵያን መመስረት ተችሏል፡፡ በአንጻሩ የባሕር በሯን በተነጠቀችባቸው ዘመኖች ኢኮኖሚዋ የኮሰሰ ባሕሏ የደበዘዘ፣ ፖለቲካዋ የተናጋ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ አይተናል፡፡
በኢትዮጵያ እጅግ አንጸባራቂ የነበረው የአክሱም ሥልጣኔ እንዲያ መግነኑ በሌላ አጋጣሚ ሳይሆን፤ አክሱም በቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ በገነባችው የበላይነት ምክንያት ነበር፡፡
አዱሊስን ዋና በር በማድረግ በወቅቱ በነበረው ዓለም አቀፋዊ ንግድ በግንባር ቀደምትነት በመሳተፏ አክሱም እስካሁን የሚያስደንቀውን ሥልጣኔ መገንባት ቻለች፡፡” ብለዋል፡፡
በመሆኑም፤ የባሕር በርና ደህንነት ሊነጣጠሉ የማይችሉ ነገሮች በመሆናቸው ኢትዮጵያ የራሷን ደህንነትና ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባሻገር በቀጣናው ያላትን የሰላም ማስከበር ሚና በአግባቡ እንድትወጣ የባሕር በር ባለቤትነት መብቷ መረጋገጥ ይሻል፡፡
በቤተልሔም ግርማ