አዲስ አበባ የከተማ ልማት ምሳሌ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ በቅርብ ዓመታት ያካሄደችው አጠቃላይ የመሰረተ ልማት እና የከተማ ገጽታ ግንባታ ለሌሎች ከተሞች አርአያ አድርጓታል፡፡
መዲናዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ዘመናዊ እና ጽዱ ለማድረግ የተሰሩት ሰፊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የዚሁ ትልቅ ስኬት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆኑ፤ በአፍሪካ 10 ጽዱ ከተሞች ውስጥ እንድትመደብ ከፍተኛ ሚና አላቸው።
ይህ ለውጥ በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ እና የጥራት ደረጃ መጠናቀቁ፤ አዲስ አበባን በፈጣን እድገት ላይ የምትገኝ እና ምሳሌ የምትሆን የአፍሪካ መዲና አድርጓታል።
በከተማዋ በተተገበረው በዚህ አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍኑ ሰፋፊ መንገዶች፣ የብስክሌት እና የእግር መንገድ መስመሮች እንዲሁም ሰፊ የሕዝብ ትራንሰፖርት ተርሚናሎች ተገንብተዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በመዲናዋ ከ60 ሺህ በላይ እንዲሁም በ2018 ዓ.ም ብቻ 20 ሺህ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ይበልጥ አዲስ አበባን የለውጥ ማዕከል አድርገዋታል።
በተጨማሪም አረንጓዴ ስፍራዎችን የማስፋፋት ሥራው ከተማዋን ለጤና ተስማሚነትን ከማሻሻል ባለፈ 2 ነጥብ 8 በመቶ የነበረውን የደን ሽፋን ወደ 24 በመቶ አሳድጎታል፡፡
የተቀናጀ የፍሳሽ እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታው ደግሞ የከተማዋን የረጅም ጊዜ ዘላቂነት ያረጋግጣል።
የዚህ የልማት ጉዞ ሌላው ዋና ትኩረት ሰብዓዊነትን እና ማህበራዊ ፍትህን መሰረት ያደረገ መሆኑ ነው፡፡
በልማቱ ሂደት በሺዎች የሚቆጠሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች የተሻለ እና ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ማግኘት የቻሉ ሲሆን፤ የቆዩ እና ለኑሮ የማይመቹ የመኖሪያ መንደሮችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ታድሰው ለዜጎች ምቹ ሆነዋል፡፡
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ለብዙ ሺህ ወጣቶች እና ስራ ፈላጊዎች አዲስ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ንቅናቄ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
በከንፍረንስ ቱሪዝም ረገድ በ2018 ዓ.ም ብቻ አዲስ አበባ 220 ዓለም ዓቀፋዊና አሁጉራዊ መድረኮችን በማስተናገድ የትኩረት ማዕከልነትን አግኝታለች።
በአጠቃላይ አዲስ አበባ ያስመዘገበችው ፈጣን እና ጥራት ያለው የልማት ሥራ፣ ከተሞች እንዴት በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን ማደስ እንደሚችሉ ያሳየ ተግባራዊ ትምህርት ነው።
የከተማዋ አመራር እና ነዋሪዎች የተቀናጀ ጥረት ውጤት የሆነው ይህ ስኬት፤ ዛሬ ላይ በርካታ የክልል ከተሞች እና የአፍሪካ መዲናዎች ልምድ የሚቀስሙበት እና ተሞክሮ የሚወስዱበት የከተማ ልማት ምሳሌ ለመሆን በቅቷል፡፡
በአብረሃም አበራ