አምራች ኢንዱስትሪ፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር ፍልስፍና ሀገር በቀል አቅምን በማስተባበር፣ ያለፉ ስኬቶችን በማስቀጠልና ስህተቶችን በማረም የተሟላ እና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማምጣትን ያለመ ነው።
በዚህ እይታ ውስጥ ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ሽግግር ቁልፍ ከሆኑ ዘርፎች መካከል አምራች ኢንዱስትሪው ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል።
የመደመር መንግሥት በአምራች ዘርፉ ላይ ያስተዋወቀው ዋነኛው ተሞክሮ “ያኢትዮጵያ ታምርት” የተሰኘው ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
ይህ ንቅናቄ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ማነቆዎች በመለየት እና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡
ቀደም ሲል ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይገቡ የነበሩ የጨርቃጨርቅ፣ የሲሚንቶ፣ የብረታ ብረት፣ የምግብና መጠጥ እንዲሁም የመድኃኒት ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም እንዲያድግ ተደርጓል።
በተጨማሪም በተለያዩ የመሰረተ ልማትና የጥሬ ዕቃ እጥረት ምክንያት የማምረት አቅማቸው ተዳክሞ የነበሩ በርካታ ፋብሪካዎች ወደ ሙሉ የማምረት አቅማቸው እንዲመለሱ የተቀናጀ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
በመደመር እይታ ኢዱስትሪዎችን በተበታተነ ሁኔታ ከመገንባት ይልቅ የተሻለ የመሰረተ ልማት እና የአገልግሎት ማዕከል ባላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ማደራጀት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማምጣት እና ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚላኩ ምርቶችን በማብዛት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን አሳድገዋል።
በእነዚህ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ምክንያት ለወጣቶች እና ለሴቶች የስራ እድሎች ተፈጥረዋል።
ግብርናን ከኢንዱስትሪ ጋር ለማስተሳሰር በተገነቡ የተቀናጁ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች አማካኝነት የሀገር ውስጥ የግብርና ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ተደርጓል።
አምራች ኢንዱስትሪው ያለግል ዘርፉ ንቁ ተሳትፎ ማደግ እንደማይችል በመደመር ፍልስፍና ይታመናል። በመሆኑም የግል ዘርፉን የሚያበረታቱ በርካታ የመዋቅር እና የፖሊሲ ርምጃዎች ተወስደዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ቅድሚያ የሚሰጥ የብድር አቅርቦት እና የውጭ ምንዛሬ ክፍፍል አሰራርን ለማሻሻል ጥረቶች ተደርገዋል።
የንግድ ፈቃድ፣ የጉምሩክ እና የግብር አሰራሮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ለባለሀብቶች ምቹ የንግድ ስነ ምህዳር የመፍጠር ስራዎች ተከናውነዋል።
የኃይል አቅርቦትን በቂነት ለማረጋገጥ ከተሰሩት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ታዳሽ የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክቶች በተጨማሪ፤ የሎጂስቲክስ አማራጮች እንዲሰፉ ተደርጓል።
በመደመር መንግሥት የተከናወኑ ስራዎች የኢትዮጵያን አምራች ዘርፍ ከተራ የጥሬ ዕቃ አቅራቢነት እሴት ጨምሮ ወደማምረት ሽግግር እንዲያደርግ መሰረት ጥለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት የገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሬ ጫናን ለመቀነስ የጎላ ሚና ተጫውተዋል።
አምራች ኢንዱስትሪው አሁን የያዘውን የእድገትና የሽግግር ጉዞ አስቀጥሎ ማስኬድ ከተቻለ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
በመልካም ፈቃዱ