ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ 3ኛ የመስቀል ደመራ በዓልን ለመታደም አዲስ አበባ ገብተዋል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ 3ኛ የመስቀል ደመራ በዓልን ለመታደም አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግብዣ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ ለመጡት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ 3ኛ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ÷ በኢትዮጵያ መልካም ቆይታ እንዲኖራቸው ተመኝተዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ 3ኛ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያን ልዩ የመስቀል ደመራ በዓል ለማክበር በመጋበዛቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሁለቱ እህትማማች አብያተ ክርስቲያናት ጥንታዊ አንድነታቸውን፣ የሀገራቱን ባህል፣ እውቀት እና እሴት በማጠናከር አጋርነታቸውን እንደሚቀጥሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በበጸሎት መንገሻ