Fana: At a Speed of Life!

እንደ ደመራው በጋራ ስንቆም ለሀገራችን ጨለማውን የሚያሸንፍ ብርሃን እንሆናለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደ ደመራው በጋራ ስንቆም ለሀገራችን ጨለማውን የሚያሸንፍ የማይበገር ብርሃን እንሆናለን አሉ።

የመስቀል ደመራ ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ በድምቀት እየተካሄደ ነው።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከተማችን አዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓለም ስበት ማዕከል፣ የንጽህና ተምሳሌት እንዲሁም በአጭር ጊዜ የተከናወነ የከተማ ለውጥ ምሳሌ ሆናለች ብለዋል።

በከተማችን እንደመስቀል ዓይነት ታላላቅ በዓላትን ስናከብር ከበዓሉ በሻገር የሀገራችንን ገጽታ እየገነባን እንግዳ ተቀባይ ጨዋነታችንን እያሳየን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህም በርካታ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ ሲመጡ በእንግዳ ተቀባይነት እየተስተናገዱ የኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነት መገለጫ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተማችን ታላላቅ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ኩነቶች እና በዓላትን በስኬት የመምራት እና የማስተናገድ ዓቅሟ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል ነው ያሉት።

ይህ የሆነው ከተማችንን በጋራ ስለገነባን በየጊዜው ስበቷ እንዲጨምር ማድረግ ችለናል ሲሉ ተናግረዋል።

የተለያዩ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሀይማኖት እንዲሁም ማንነት ቢኖረንም እንደ ደመራው በጋራ ስንቆም እጅ ለእጅ ተያይዘን ስንራመድና ህብረታችንን ስናጠናክር ለከተማችንም ሆነ ለሀገራችን ጨለማውን የሚያሸንፍ የማይበገር ብርሃን እንሆናለን ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.