ለአንድነታችን እንቅፋት የሆኑብንን በአርቆ አሳቢነት በማለፍ ለሀገራዊ ሰላም አበክረን ልንሰራ ይገባል – ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአንድነታችንና ለእድገታችን እንቅፋት የሆኑብንን በአርቆ አሳቢነት በማለፍ ለተሟላ ሀገራዊ ሰላም አበክረን ልንሰራ ይገባል አሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፡፡
የመስቀል ደመራ ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ በድምቀት እየተካሄደ ነው።
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት፤ የመስቀሉ ትልቁ መልዕክት ሰላምና አንድነትን፣ ይቅርታን እና እርቅን እንዲሁም ፍቅርንና ስምምነትን በሰው ልጆች ሁሉ ማስፈን ነው ብለዋል፡፡
ለአንድነታችንና ለእድገታችን እንቅፋት የሆኑብንን ሁሉ በትዕግስትና በአርቆ አሳቢነት በማለፍ ለተሟላ ሀገራዊ ሰላምና አንድነት አበክረን ልንሰራ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በአከባበር ስነስርዓቱ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የውጭ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች፣ የእምነቱ ተከታዮችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።