Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያና ህንድ መካከል ያለው የጠበቀ ግንኙነት በትብብር ለመስራት የጎላ ፋይዳ አለው – አቶ መሀመድ እድሪስ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ በኢትዮጵያ እና ህንድ መካከል ያለው ዘመናትን ያስቆጠረ የጠበቀ ግንኙነት በትብብር ለመስራት የጎላ ፋይዳ አለው አሉ።

ሚኒስትሩ ለመስቀል በዓል ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ 3ኛ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

አቶ መሀመድ እድሪስ በወቅቱ እንዳሉት፤ በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች እና አብያተ ክርስቲያናት መካከል ዘመናትን ያስቆጠረ፣ ሰላማዊ አብሮነትን ያጎላ የጠበቀ ግንኙነት አላቸው።

ይህ ለዓለም ምሳሌ የሆነው የጠበቀ ግንኙነት በትብብር ለመስራት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ 3ኛ በበኩላቸው፤ በቅዱሳት መጻሕፍት በተደጋጋሚ ወደ ተጠቀሰችው ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ደስታ እና ክብር እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

በሕንድ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እህት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ግንኙነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑን አስታውሰዋል።

ይህ ግንኙነት በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በሀገራቱ መካከል ለሚኖረው ታላቅ የወደፊት ተስፋ ማረጋገጫ መሆኑን መናገራቸውን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.