የዜጎችን ተጠቃሚነት ያሳደገው ሰው ተኮር ልማት፡ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገራችን ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተከናወኑ አጠቃላይ የልማትና የማሕበራዊ አገልግሎት ሥራዎች የመደመር መንግሥት ትኩረት ከሰጠባቸው ጉዳዮች ዋነኛው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ሕይወት ማሻሻል ነው።
በመላው ኢትዮጵያ በተተገበሩ ሰው ተኮር ሥራዎች የበርካታ ዜጎችን ሕይወት በላቀ ደረጃ መለወጥና ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
የገጠርና ከተማ የማሕበራዊ ደህንነት፣ የሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በቀጥታ ድጋፍና በግብርና ላይ በማሳተፍ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
አቅም አጠር የሆኑ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች የቀጥታ የገንዘብና የምግብ ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ሲሆን÷ መስራት የሚችሉ ዜጎች ደግሞ በሕዝብ የልማት ሥራዎች በማሰማራት ዘላቂ የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩ ተደርጓል።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የከተማ ነዋሪዎች በከተማ ግብርና ማለትም በጓሮ አትክልት፣ በዶሮ እርባታና በከብት ማደለብ ሥራዎች በመሰማራት የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡና ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
በከተሞችና በገጠር ነዋሪዎችን ማዕከል ያደረጉ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ትልቅ ስኬት አስመዝግበዋል።
በበጋና በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ቤቶች ታድሰዋል፤ አዲስ ቤቶችም ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተላላፈዋል።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችና የጎዳና ተዳዳሪዎች በቀን አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ገንቢ ምግብ የሚያገኙባቸው የሕዝብ መመገቢያ ማዕከላት መስፋፋታቸው ከፍተኛ ማህበራዊ እፎይታን ፈጥሯል።
በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ት/ቤቶች የተዘረጋው የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች በመጡ ልጆች ዘንድ የትምህርት ማቋረጥን ከመቀነሱም በላይ የተማሪዎችን ጤንነትና የትምህርት አቀባበል አሻሽሏል።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ከአቅማቸው በላይ የሆነ የሕክምና ወጪ ሳይፈታተናቸው በነፃ ወይም በአነስተኛ ክፍያ ደረጃቸውን የጠበቁ የሕክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ተደርጓል።
በአጠቃላይ በመላው ኢትዮጵያ የተተገበሩት ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት ከማሻሻል ባሻገር ማህበራዊ ፍትሕን ለማረጋገጥና የሕብረተሰቡን የእርስ በርስ የመደጋገፍ ባሕል ለማጠናከር ትልቅ መሰረት ጥለዋል።
እነዚህ ስኬቶች ተጠናክረው ሲቀጥሉ የመደጋገፍ እሴትን በማሕበረሰቡ ውስጥ ከማስረጽ ባሻገር የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞ ያፋጥናሉ።
በመልካም ፈቃዱ