Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በላቀ ቁርጠኝነት ይሰራል – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀረሪ ክልል የሕዝቡን ህይወት የሚያሻሽሉ የልማት ሥራዎችን በማከናወን የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በላቀ ቁርጠኝነት እንሰራለን አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ።
የክልሉ ምክር ቤት 7ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መስራች ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በድጋሚ የተሰየሙት አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፤ ባለፉት 5 ዓመታት ያጋጠሙ ፈተናዎችን በመሻገር ክልሉንና ሕዝቡን ወደ ብልፅግና ያመሩ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል።
የፖለቲካ ባህላችን ከተንኮልና ጥላቻ ወጥቶ በሀሳብ የበላይነት ላይ እንዲመሰረት በመደረጉም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ አበረታች ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል ብለዋል።
በአዲሱ ምክር ቤት 4 የተፎካካሪና አንድ የግል እጩ ተወዳዳሪዎች በህዝብ ተመርጠው የምክር ቤት አባል መሆናቸውም የፖለቲካ ባህላችን በተጨባጭ መለወጡን የሚያሳይ እንደሆነም አመልክተዋል።
የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ፣ የትምህርትና ጤና አገልግሎት ጥራት እንዲረጋገጥ እና በኮሪደር ልማቱ ሀረር ለኑሮ የምትመች ከተማ እንድትሆን ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
ከዚህ ባሻገርም የሀረር ከተማን በዓለም አቀፍ መድረኮች እውቅና እንድታገኝ ከማስቻል ባሻገር በግብርናና ሌማት ትሩፋት ዘርፎች ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ አበረታች ውጤቶች ተመዝግቧል ነው ያሉት።
ባለፉት 5 ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ከማድረግ ባሻገር ለክልሉ እድገትና ልማት መሠረት የሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ ይሰራልም ብለዋል።
በክልሉ ፈጣንና ፍትኃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን ከማከናወን በተጨማሪ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ የህዝቡ ህይወት እንዲሻሻል በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም አስረድተዋል።
በክልሉ የከተማና ገጠር የኮሪደር ልማቶችን በላቀ ጥራትና ፍጥነት ለማከናወን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ የዜጎች የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም አንስተዋል።
በሌላ በኩል በመንግሥት ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች ፈጣን፣ ፍትኃዊ እና ከብልሹ አሰራር የፀዱ እንዲሆኑ በማስቻል የዜጎችን እርካታ ለማሳደግ በላቀ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በተስፋዬ ኃይሉ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.