ኢሬቻ፡ የምስጋና፣ የይቅርታና ሕብረ ብሔራዊነት መገለጫ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ የክረምት ወቅት በሰላም መጠናቀቁን ተከትሎ ሁሉን ነገር ለፈጠረው ፈጣሪ (ዋቃ) ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው።
በዓሉ ለፈጣሪ ምስጋና ከማቅረብ ባለፈ፣ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ቁርኝት፣ የማኅበረሰብ እሴቶችንና የጋራ ሕይወትን የሚያሳይ ሥነ ሥርዓት ነው።
በዚህ ሥርዓት ውስጥ ኢሬቻ ምስጋናን ከማቅረብ ባለፈ ሰዎች የተራራቁ ግንኙነቶችን እንዲያድሱ፣ የተቀያየሙ ሰዎች እንዲታረቁና ማኅበረሰቡ በአንድነት አዲሱን ወቅት እንዲቀበል የሚያግዝ ማኅበራዊ መድረክ ሆኖ ይገለጻል።
በክረምት ወቅት በዝናብ፣ በወንዞች ሙላትና በሌሎች የተፈጥሮ ሁኔታዎች ምክንያት ቤተሰቦችና ዘመድ አዝማዶች ተራርቀው ሊቆዩ ይችላሉ። የዝናብ ወቅት ሲያልፍ ግን ወንዞች ይረጋጋሉ፣ መንገዶች ይከፈታሉ፣ ተራርቀው የነበሩ ሰዎችም ይገናኛሉ።
በዚህ ተፈጥሯዊ ሒደት ውስጥ ኢሬቻ ልዩ ትርጉም ይይዛል። ከክረምት ወደ ብርሃን፣ ከመራራቅ ወደ መቀራረብ፣ ከቂም ወደ ይቅርታና ከግጭት ወደ ሰላም የሚደረግ ሽግግርን እንደሚያመለክት አባገዳዎች ይናገራሉ፡፡
የኢሬቻ ታዳሚዎች አረንጓዴ እርጥብ ሣርና አበባ ይዘው ወደ ሆራ፣ ማለትም በዓሉ ወደ ሚከበርበት የውኃ ዳርቻ ያቀናሉ። በዚያም በመሰባሰብና በሕብረት ለፈጣሪ (ዋቃ) ምስጋና ያቀርባሉ፤ ለመጪው ዘመንም ሰላምና በረከትን ይመኛሉ።
በዚህ ሥነ ሥርዓት የተፈጥሮ መልሶ መታደስ ከሰው ሕይወት መታደስ ጋር ተያይዞ ይታያል። አረንጓዴ ሣርና አበባ የአዲስ ወቅትና የተስፋ ምልክት ሲሆኑ÷ ውኃው ደግሞ የሕይወትና የንጽሕና ምንጭነቱን ያሳያል።
ኢሬቻ የምስጋና በዓል ብቻ አይደለም። የይቅርታና የመታረቅ እሴትንም ያጎላል። በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ሰዎች ያለፈውን ቂምና ቅሬታ በመተው አዲሱን ወቅት በሰላም እንዲቀበሉ ይበረታታሉ።
ኢሬቻ ከዋና ዋና የአከባበር ሥፍራዎቹ መካከል በቢሾፍቱ የሚገኘው ሆራ አርሰዲና በአዲስ አበባ የሚገኘው ሆራ ፊንፊኔ ይጠቀሳሉ።
በዓሉ ላይ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ቄሮዎችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ። ባህላዊ ልብሶች፣ ጭፈራዎች፣ የፈረሰኞች ትርዒትና ሌሎች ባህላዊ ክዋኔዎች የበዓሉን ድምቀት የሚያጎሉ ክዋኔዎች ናቸው፡፡
ኢሬቻ የባህል ልብስ፣ ጭፈራ፣ ዝማሬና ሌሎች ክዋኔዎች የሚታዩበት በዓል ነው። በተለይ በዓሉ በትልልቅ የአከባበር ሥፍራዎች ሲከበር የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትን የለበሱ ታዳሚዎች የበዓሉን ድምቀት ምልዑ ያደርጉታል።
ይህ የአከባበር መልክ የውበት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የባህል ልብሶች፣ የሥነ ሥርዓት ቅርጾች፣ ዝማሬዎችና ባህላዊ ዕውቀቶች ከአዛውንት ወደ ወጣት እንዲተላለፉ የሚያደርጉ የባህል መሸጋገሪያዎች ናቸው።
ኢሬቻ በዚህ መልኩ ያለፈውን ከዛሬ ጋር፣ ዛሬንም ከነገ ጋር የሚያገናኝ ሕያው ባህላዊ ቅርስ ሆኖ ይቀጥላል። የምስጋና ሥነ ሥርዓቱ፣ የይቅርታና የእርቅ እሴቱ፣ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ቁርኝትና የአብሮነት መልዕክቱ በየዓመቱ በአዲስ ትውልድ ይታደሳሉ።
ኢሬቻ የአንድ ቀን በዓል ብቻ ሳይሆን፣ ምስጋናን፣ ይቅርታን፣ እርቅን፣ ሰላምን፣ አብሮነትን፣ የተፈጥሮ ክብካቤንና የባህል ቅብብሎሽን በአንድ ላይ የሚያስተሳስር ትልቅ ባህላዊ ትሩፋት ነው።
የዘንድሮው ኢሬቻ “ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሃሳብ በሆረ ፊንፊኔ ነገ መስከረም 23 እንዲሁም በሆረ ሃርሰዴ መስከረም 24 ቀን 2019 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በድምቀት ይከበራል።
ነገ በአዲስ አበባ ለሚከበረው የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ለመሳተፍ ከተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ እንግዶችና ተሳታፊዎች ወደ ከተማዋ ገብተዋል፡፡
ወደ ከተማ ለገቡ ተሳታፊዎች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተለያዩ አካባቢዎች በወዳጅነት እና በአብሮነት አቀባበል አድርገዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ