Fana: At a Speed of Life!

የህዝብን ችግር የሚያዳምጥ እና በፍጥነት የሚፈታ መንግሥት ለመገንባት ይሰራል – ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራትን (ዶ/ር)

የህዝብን ችግር የሚያዳምጥ፣ ችግሮችን በፍጥነት የሚፈታና ለሥራው ተጠያቂነትን የሚወስድ መንግሥት ለመገንባት ይሰራል አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)።
“7ኛ ዙር መስራች ጉባኤውን በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ የሚገኘው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)ን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሰይሟል።
ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራትን (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የምግብ ሉዓላዊነትንና የኢኮኖሚ ሽግግርን ማሳካት፣ የሰው ሃብት ልማትን ማስፋፋት፣ መሰረተ ልማትን ማስፋፋትና የመንግስትን ተጠያቂነት ማጠናከር ዋና ትኩረቶች እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
ሰላምና ደህንነት የመጀመሪያና ዋነኛ ትኩረት እንደሚሆን የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ ሰላም ለልማትና ለህዝቡ ብልጽግና መሰረት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የክልሉን የጸጥታ መዋቅር ከማጠናከር ባለፈ የግጭቶችን መንስኤ በመለየት፣ በውይይትና በህዝባዊ ምክክር፣ በሀገር ሽማግሌዎች ሚናና በህግ ማስከበር ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የክልሉን የግብርና አቅም በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ሌላው ዋነኛ ትኩረት መሆኑን በማንሳት የግብርና ግብዓቶችን አቅርቦት ማሻሻል፣ መስኖንና ዘመናዊ ግብርናን ማስፋፋት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና አርሶ አደሩ ከራስ ፍጆታ በላይ ለገበያ እንዲያመርት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚሰራ አመልክተዋል።
በተጨማሪም ለግሉ ዘርፍ ምቹ የንግድ አካባቢ በመፍጠር፤ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝም፣ በዲጂታል ኢኮኖሚና በሌሎች የንግድና የአገልግሎት ዘርፎች አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች እንዲቋቋሙና የሥራ እድል እንዲስፋፋ ይሰራል ብለዋል።
ወጣቶችና ሴቶች የልማት ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ዋና ውሳኔ ሰጪዎችና የልማቱ መሪዎች እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠርም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ትምህርትና ጤና የመንግስታቸው ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያገኙ በማንሳት በትምህርት ዘርፍ የአስተማሪዎች ብቃትን፣ የትምህርት ጥራትንና የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል፤ በጤና ዘርፍ ደግሞ በቅድመ መከላከልና በጤና አገልግሎት ጥራት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በክልሉ የተጀመሩ የመንገድ፣ የመብራት፣ የቴሌኮምና የውኃ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት ማጠናቀቅ ሌላው ትኩረት እንደሚሆን ገልጸው የመሠረተ ልማት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም በጥናት ላይ የተመሰረተ የማስፋፋት ስራ እንደሚከናወን አብራርተዋል።
የክልሉ ልማት በጥቂት የከተማ ማዕከላት ብቻ እንዳይወሰን በርካታ ከተሞች በእቅድ እንዲስፋፉና እንዲያድጉ፣ ከተማና ገጠር ተሳስረው እንዲለሙ እንደሚሰራ እንዲሁም በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችም እንደሚጠናከሩ አስረድተዋል።
የመንግሥት ውጤታማነት የሚለካው በንግግር ሳይሆን በዜጎች ህይወት ላይ በሚመጣው ተጨባጭ ለውጥ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ የህዝብን ችግር የሚያዳምጥ፣ ችግሮችን በፍጥነት የሚፈታና ለሥራው ተጠያቂነትን የሚወስድ መንግሥት ለመገንባት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የክልሉን ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የምክር ቤት አባላት፣ የክልሉ አመራሮች፣ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የክልሉ ተወላጆች፣ ዲያስፖራዎች፣ ባለሀብቶችና መላው የክልሉ ህዝቦች በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ ጌትነት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.