Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ንግድ ኮንቨርጀንስ ጉባዔን እንድታዘጋጅ ተመረጠች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2027 የሚካሄደውን የአፍሪካ የንግድ ኮንቨርጀንስ ጉባዔ እንድታስተናግድ ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
በዛምቢያ በተካሄደው የአፍሪካ የንግድ ኮንቨርጀንስ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ባቀረበችው የጨረታ ሰነድ አሸናፊ በመሆኗ ጉባዔውን ለማዘጋጀት ተመርጣለች፡፡
ጉባዔውን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የተከናወነውን የጨረታ ሒደት የኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ባለሙያዎች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ማህበር እንዲሁም የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስና ሰፕላይ ቼይን ማህበር በቅንጅት መርተውታል።
በውሳኔው መሠረት አዲስ አበባ ጉባዔውን የምታስተናግድ ሲሆን÷ ከአፍሪካ የሚሰበሰቡ ባለሙያዎች፣ ኤክስፐርቶች፣ የንግድ ዘርፍ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የልማት አጋሮች ይሳተፋሉ፡፡
ይህም ኢትዮጵያ ያላትን ዘርፈ ብዙ አቅም ለማሳየትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ፍሬያማ ትስስር ለመፍጠር ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቅሷል።
የቲኮን አፍሪካ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ጎው እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ አዘጋጅ ሆና መመረጧ የሀገሪቱ የሙያ ማህበራት ያላቸውን ጥንካሬ እና በአፍሪካ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ እያደገ የመጣውን ሚና የሚያሳይ ነው።
በመላው አህጉሪቱ ፈጠራን፣ ትብብርንና ዘላቂ ልማትን የሚያጎለብት ጉባዔ ለማዘጋጀት ከኢትዮጵያውያን አጋሮች ጋር አብሮ ለመሥራት መዘጋጀታቸውንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የማርኬቲንግ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ፋና አባይ በበኩላቸው÷ ይህ ስኬት በሀገር ውስጥ ማህበራት መካከል የተፈጠረው ቅንጅት ፍሬ ማፈራቱን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
በዘመን በየነ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.