ለምን ዓባይ ተገደበ ? ባህር በር ለምን ጠየቃቹሁ ? የኢትዮጵያ ታላቅ ርዕይ በፈተናዎች እቶን አልፏል !
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የትልቅ ሀገር ፣ የትልቅ ህዝብ እና ታላቅ ርዕይ እናት ናት ፤ የረጅም ዘመን ስልጣኔ ባለቤት ዛሬም እንደ ትላንቱ በታሪካዊ ፈተናዎች እና በጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች መገናኛ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች።
ትላንት በአድዋ አውድማ የጥቁር ህዝብ የነጻነት ቀንዲል ሆና የበራችው ይህች ሀገር፣ ዛሬ ደግሞ የኢኮኖሚ ነጻነቷን ለማወጅ እና የልጆቿን የጨለማ ህይወት በብርሃን ለመቀየር በራሷ አቅም አዲስ ታሪክ እየጻፈች ነው።
የዓባይ መገደብ እና የባህር በር ጥያቄ የቅንጦት ፍላጎቶች ሳይሆኑ፣ የሀገሪቱ የህልውና እና የሉዓላዊነት መገለጫዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው ዘመናት ሁሉ ትልቁ ፈተናዋ ዓባይ ሲሆን፣ ሌሎቹ ፈተናዎች የዚህ ውላጅ መሆናቸውን የታሪክ ሂደት ያረጋግጣል።
ይህንን ታሪካዊ ፈተና ለመቀልበስ የተገነባው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተሟላ አኳኋን ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር፣ የኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲካ ኩስመና ታሪክ በተግባር አበቃ። ይህ ታላቅ ጉዞ የተቃኘው በድሆች እናቶች ቁጠባ፣ በደመወዛቸው ላይ በቆረጡ የመንግስት ሰራተኞች፣ በገበሬው፣ በነጋዴው እና በሀገር ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ በላብና በእንባ ነው።
ይባስ ብሎ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር በየግንባሩ ደማቸውን ለሚያፈሱላት ጀግኖች ልጆቿ ምስጋና ይግባና፣ ግድቡ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያውያን የጽናት ማማ እና በደም የተገነባ የክብር ማህተም ሆኖ ቆሟል።
ከዚህ የኃይል ሉዓላዊነት ጎን ለጎን፣ ኢትዮጵያን በጂኦግራፊ እስረኝነት ውስጥ አቆይቶ የመቀጠል ፍላጎት ከተፈጥሮ ህግ ጋር የሚጋጭ መሆኑን የመሪዎቿ ስትራቴጂካዊ እይታ ያመላክታል። የታሪክ መዳረሻችን እና የሕልውና መሠረታችን ቀይ ባሕር እና ዓባይ በመሆናቸው፣ ቀይ ባህር እና ኢትዮጵያ ለዘላለም ተነጣጥለው መኖር አይችሉም።
ያልተመረጠ እና ያልተወያየ መንግሥት በፈጠረው ሸፍጥ ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ብትሆንም፣ ይህ የተፈጠረው ስህተት የትናንትና ታሪክ በመሆኑ ነገ መታረሙ የማይቀሬ ሀቅ ነው። ይህ ጥያቄ የሌሎችን ሉዓላዊነት በመጋፋት ሳይሆን በጋራ ልማት መርህ ላይ የተመሰረተ ነው።
ኢትዮጵያ “ስጡን ብቻ” ሳትል “ከእኛም ውሰዱ” በሚል መርህ የምትሻው የጋራ መተንፈሻ በር ብቻ ነው።
ነገር ግን ይህ የታሪክ ስህተት ሲታረም እና የኢትዮጵያ ትንሳኤ ሲበሰር የማይዋጥላቸው የካይሮ ሴረኞች እና ቀጣናዊ ተላላኪዎቻቸው የጥፋት ከበሮ በመደለቅ ላይ ይገኛሉ።
ካይሮ፣ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን እንደ ቅዱስ መጽሐፍ እየጠቀሰች፣ የወንዙ ብቸኛ ባለቤት ለመሆን የምታደርገው የዲፕሎማሲ ግብግብ አልሳካ ሲላት ዛሬ ቀጣናውን ወደ ግጭት ቀጠና ለመቀየር እየተጋች ትገኛለች።
የራሷን የውስጥ ፖለቲካዊ ቀውስ ለመሸፈን ሲባል፣ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ ተላላኪዎቿን በማስታጠቅ ቀጣናውን ወደ እሳት አደጋ ለማምራት ትሞክራለች። ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ዙሪያ ሁልጊዜም በሰላማዊ መንገድ መነጋገርን የምታስቀድም እና ውጊያን የማትመርጥ ቢሆንም፣ ይህ የሰላም ፍላጎት ግን ከፍርሃት የመነጨ አይደለም። ሰላማዊና የጋራ ልማትን ብንሻም፣ ኢትዮጵያ ራሷን የመከላከል እና ሉዓላዊነቷን የማስከበር ሙሉ እና አስተማማኝ አቅም አላት።
ለኢትዮጵያ መሰል ፈተናዎች አዲስ አይደሉም። ታሪኳ በወራሪዎች፣ በውስጥ ባንዳዎች እና በውጭ ሴረኞች ተከቦ የኖረ ቢሆንም፣ በየዘመናቱ የተደቀኑባትን የሞትና የሽረት አደጋዎች ሁሉ በአሸናፊነት የመወጣት ድንቅ ተፈጥሮ አላት።
ኢትዮጵያ ልክ እንደ ወርቅ ናት፤ በእሳት እቶን ውስጥ ባለፈች ቁጥር ይበልጥ እያበራች እና እየጠነከረች ትወጣለች። የዛሬውም የዲፕሎማሲያዊ እና የወታደራዊ ከበባ ሙከራ፣ የኢትዮጵያውያን የውስጥ አንድነት ከማጠናከር ውጭ የሚያመጣው አንዳችም ፋይዳ አይኖርም።
የኢትዮጵያ ትልቅነት በጥልቀት የሚያስብ፣ በብስለት የሚራመድ እና ታሪክን የሚዋጅ ህዝብ ስላላት ነው።
ዛሬ የምታሳየው የዲፕሎማሲያዊ ብስለት እና የፅናት አቋም፣ ነገ ሀገሪቱ በምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክ የምታገኘውን ታላቅ ከፍታ የሚያመላክት ነው።
ጠላቶቿ እና ተላላኪዎቿ የጥፋት ከበሮ ቢደልቁም፣ የኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የዕድገት ብርሃን ግን ማንም ሊያጠፋው በማይችል መልኩ በርቷል። ምክንያቱም ይህች ሀገር የፈጣሪ እጅ ያለባት፣ በልጆቿ መስዋዕትነት የምትኖር እና ሁሉንም ፈተናዎች በአሸናፊነት የመወጣት የታሪክ አደራ ያለባት የጽናት ምድር ናት!
በኃይለኢየሱስ መኮንን