የምክረ ሃሳቦች ርክክቡ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሀገራዊ ፈተናዎች በራሳችን ለመፍታት ያለንን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአጀንዳ ነጥቦች እና ምክረ ሃሳቦች ርክክቡ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሀገራዊ ፈተናዎች በራሳችን ሀገር በቀል የመፍትሔ አምጭ እሴቶች ለመፍታት ያለንን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ፥ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የተገኙ የአጀንዳ ነጥቦች እና ምክረ ሐሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለፌደራል መንግሥት እንዲሁም ለክልል መንግሥታት በይፋ ርክክብ የተደረገበትን መርሃ ግብር ዛሬ ተከታትያለሁ ብለዋል።
ይህ የሰነድ ርክክብ ሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ ጉልህ ምዕራፍ የሚያስመዘግብ ነው ሲሉም አመልክተዋል።
አክለውም ይህ መድረክ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሀገራዊ ፈተናዎች አካታች በሆነ ውይይት፣ በሰላማዊ ምክክር እና በራሳችን ሀገር በቀል የመፍትሔ አምጭ እሴቶች ለመፍታት ያለንን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።