ኢትዮጵያን ከባሕር በር ነጥሎ ማቆየት አይቻልም – አቶ አባዱላ ገመዳ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያን ከባሕር በር ነጥሎ ማቆየት አይቻልም ሲሉ የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ባሕር በር እንድታጣ የተደረገው ምንም አይነት ውይይት ሳይደረግበት በጥቂት ግለሰቦች ውሳኔ መሆኑንም አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ለዘመናት ኢትዮጵያን የባሕር በር የማሳጣት ዕኩይ ሴራ ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በአውደ ውጊያ በተደጋጋሚ ጊዜ ባደረጉት ሙከራ ማሸነፍ እንደማይችሉ ሲረዱ የውስጥ ባንዳ ፈጥረው ተጠቅመውበታል ነው ያሉት።
ለዚህም ከሻዕቢያና ሕወሃት መመስረት ጀርባ የግብጽ እጅ እንደነበረበት በማሳያነት አንስተዋል፡፡
ታሪካዊ ጠላቶች በውስጣችን የፈጠሯቸው ኃይሎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንደዋዛ ተላልፎ እንዲሰጥ አድርገዋል ነው ያሉት።
በባሕር በር ጉዳይ ላይ ያደረግናቸው፣ የተግባባንባቸው በሕጋዊ መድረክ ውይይት ተደርጎ የተወሰነ ውሳኔ የለም ብለዋል፡፡
እነዚህ ጉዳዮች ሕጋዊ መንግሥት በሌለበት ሁኔታ መፈጸማቸውን አንስተው፤ በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግሥት ሕገ መንግሥት ሳይጸድቅ ምንም ጉዳይ ላይ መወሰን የሚያስችለው ሥልጣን እንዳልነበረው አስረድተዋል።
ነገር ግን ይህንን በመጣስ ውሳኔዎቹ ውይይት ሳይደረግባቸው በጥቂት ግለሰቦች ተወስነው ተግባራዊ ሲደረጉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ትልቁ ብሔራዊ ጥቅም የሆነውን የባሕር በር ማጣት የሚያስቆጭ ታሪካዊ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ መንግሥት የባሕር በር ባለቤትነቱን ጉዳይ በሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ አካሄድ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን ከባሕር በር ነጥሎ ማቆየት አይቻልም ያሉት አቶ አባዱላ፤ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት የትኛውም አካል ሊያስቆመው የማይችል አይቀሬ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።