ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን፣ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን ዛሬ ባካሄደው 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባው ነው ያፀደቀው፡፡
ረቂቅ አዋጁ ሰፊ ጥናት የተደረገበት እና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ከተጠሪ ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ በቂ ግብአት የተገኘበት መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት መስሪያ ቤቶች በአለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የታዩትን ውስንነቶች ለመቅረፍ ረቂቅ አዋጁ እንደሚያግዝ እና የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲአዊ መብቶች እንዲከበሩና የህዝቡ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል ያግዛል ተብሏል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የተቋማትን አደረጃጀት በግልጽ ማስቀመጥ የመንግስትና የህዝብ ሃብት የስራ ኃላፊዎች በአግባብ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ ቀልጣፋና ውጤታማ አደረጃጀት በመፍጠር የተቋማትን የማስፈጸም አቅምንለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው መባሉን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡