የመደመር እሳቤ ለጋራ ሀገር
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያዊነት ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ላለው ህዝብ የጋራ መጠሪያው ነው፡፡ ሀገር የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያለው፣ የትንሹም የትልቁም፣ የባለጸጋውም የደሀውም የሁሉም ናት፡፡
ሁሉ የኔ የሚላት ኢትዮጵያ የምትገነባው ደግሞ እድል በመሰጣጠት፣ ሌሎች ሀሳባቸውን እንዲገልጹ በማድረግ፣ አቅማቸውን እንዲያወጡ መንገድ በመክፈትም ጭምር ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ደግሞ በመመካከር እና ሁሉም ለኢትዮጵያ የሚበጃትን እንደየችሎታው በማበርከት ሲችል ነው፡፡
ሀገር የምትጸናው ሁሉም የእኔ ናት የሚላትን ኢትዮጵያ መገንባት ሲቻል እንደሆነ የሚያምነው የመደመር መንግሥትም አካታችነት የተሞላበትን አካሄድ ይከተላል፡፡
የፆታ፣ የዕድሜ፣ የአካባቢና የሀይማኖት ስብጥር ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል በተፎካካሪ ፓርቲነት ሲወዳደሩ ለነበሩት ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሁሉ እድል በመስጠት በጋራ ሀገር የመገንባት ጉዞውን በተግባር አሳይቷል፡፡
ኢትዮጵያ ዘመናትን ተሻግራ እዚህ የደረሰችው፣ ሁሉም ይመለከተኛል በሚል ስለተጋ እና የባለቤትነት መንፈስን ይዞ በመቆሙ ነው፡፡ ለነገ የምንሰራት ኢትዮጵያም ልክ እንደ ትናንቱ የሁላችንን የተባበሩ ክንዶችን የምትፈልግ ናት፡፡
ሀገር የሁሉም መሆኗ በተግባር የሚተረጎመው እያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ሲችል፣ እኩል በሀገሪቷ ሀብት የመጠቀም መብት እንዲሁም የመጠበቅም ኃላፊነት ሲሰጠው ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗን ማወቅ ልክን ማወቅ ነው፤ የራስን ሳይዘነጉ የጋራ ማንነትን መውደድና ማክበር ነው። የመደመር መንግሥትም ይህን ለማረጋገጥ አካታችነትና ችሎታን አዋህዶ በተግባር እየሠራ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)የመደመር መንግሥት ካቢኔ አባላትን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት የእኛ መሻት ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፣ የሰለጠነች ሀገር፣ ዜጎቿን የሚነካ የልማት እንቅስቃሴ የምታደርግ ሀገር፣ ለሁሉ እኩል የሆነች፣ ሁሉ የኔ የሚላት የሚመኛት፣ የሚሠራት ሀገር እንድትሆን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው በጋራ ሀገር እንገነባለን ይህ ብቻ ነው ኢትዮጵያን ለማሰልጠን የሚያዋጣው መንገድ ሲሉም አመልክተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗን ማወቅና መተግበር የነገዋ ኢትዮጵያ ሰላሟ የተረጋገጠና ጠንካራ መሠረት ያላት የበለጸገች ሀገር እንድትሆን ወሳኝ ሚናን ይጫወታል፡፡
#የመደመር_መንግሥት
በቤተልሔም ግርማ