ወርቃማው የኢኮኖሚ ህዳሴ፤ የማዕድን ዘርፍ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 ()ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፉን እምቅ አቅም በመረዳት አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶዋ አድርጋ አስቀምጣለች፡፡ ይህም የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠቀም ትኩረት ሰጥታ መጓዟን የሚያሳይ ነው፡፡
ሀገሪቱ ያላትን የማዕድን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችና የህግ ማዕቀፎች ተቀርጸዋል፡፡
በተጨማሪም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን የሚቆጣጠርና የህገወጥ ንግድን የሚገቱ ፖሊሲና የህግ ማስከበር ርምጃዎችን እየተገበረች ትገኛለች፡፡ ይህም ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ መንገድ ነው፡፡
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ጋር በማቀናጀት፣ የምርምር እንዲሁም ማዕድን የማውጣት ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ከውጪ የሚገቡ ሲሚንቶን ጨምሮ ሌሎች ለኢንዱስትሪ የሚያገለግሉ ግብዓቶችን፣ የከሰል ምርትንም በሀገር ውስጥ የመተካትና የማቀናጀት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ይህም በማዕድን ዘርፉ የታየ ተጨባጭ ተግባር የኢንዱስትዎችን ምርታማነት ከማሳደግ በላቀ የውጪ ምንዛሬን ገቢን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡
መንግሥት ዜጎች በማዕድን ማውጣት ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ በማድረጉ የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም የኑሮ መሻሻል በረከትን ይዞ የመጣ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ አጋርነት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባውን ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በዛሬው ዕለት ስራ አስጀምረዋል፡፡
ማጣሪያ ፋብሪካው ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም ያለው፣ የወርቅ ጥራትን ለመለካት፣ ለማንጠር እና ለውጭ ገበያ ዝግጁ ወደሆኑ ንጹህ ወርቆች ለመቀየር፣ እንዲሁም በተለያዩ የጥራት ደረጃዎች የተሰናዱ የወርቅና የብር ጡቦች ለማምረት የሚያስችል ነው፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ግብርናን ብቻ ከተመረኮዘ የኢኮኖሚ ጥገኝነት ወጥታ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል፡፡
በቤተልሔም ግርማ