አዲሱ የመደመር መንግሥት ለኢትዮጵያ መጻኢ እድገት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታዋን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም የምታደርገው የሽግግር ምዕራፍ ነው።
ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ዓምስት ዓመታት እቅዶችዋ የሚሆናትን አዲስ የመንግሥት ምስረታ አካሂዳለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን እጩዎች ዝርዝር አቅርበው ሹመት አጸድቀዋል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ሹመቶችን ሰጥተዋል።
ይህ የተሰጠው አዲስ ኃላፊነት የሚኒስትሮችን የስራ ልምድ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የእውቀት ልኬት፣ የብቃት መጠን እና የመምራት አቅም ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡
ታዲያ በዚህ የኃላፊነት ጥሪ የተካተቱት አካላት እንዲሁ ለሹመት የታጩ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ ወደፊት ልትደርስበት ያቀደችዉን እድገት በእውቀት፣ በጉልበት የሚያግዙ እና የሚሰጣቸውን ኃላፊት ለመወጣት ብቁ የሆኑ ናቸው፡፡
የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን መጻኢ እድል የሚወስኑ የሀገርን እድገት የሚያፋጥኑ እቅድ እና ስራዎችን ሲያስተገብር ለሚያስፈልገው የሰው ሀይል በአዲስ መልኩ እና ከነበራቸው የስራ አረዳድ አንጻር እንደገና የተሾሙት የካቢኔ አባላት እና ሚኒስትሮች አዲስ የሀይል ስብስብን የፈጠሩ ናቸው፡፡
በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ፣ በፕሮጀክቶች ፍጥት እና ጥራት፣ በአገልግሎት ዘርፍ ቀልጣፋነት እና ተደራሽነት እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ኃላፊነትን ከተጠያቂነት ጋር፣ ስልጣንን ከሰብዓዊነት ጋር ሊላበሱ እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት ያነሱት ሃሳብ ነው፡፡
አዲሱ የመደመር መንግሥት የብልጽግና ጉዞውን ዳር ለማድረስ ርዕይን የመፈጸም አቅም፣ በፈተናዎች የማይበገር ተላማጅነት እንዲሁም ትውልድ አሻጋሪ የሆነውን ማኅበራዊ ውል በተግባር በማሳየት የጸናች ሀገረ መንግሥት የመገንባት ታሪካዊ አደራውን መወጣት ይጠበቅበታል።
በአጠቃላይ አዲሱ መንግሥት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን በእድገት ጎዳና ለማራመድ እና የአፍሪካ ተምሳሌትነቷን ለማስጠበቅ ያለው ፋይዳ ወደፊት በስራ የሚገለጽ እና አመርቂ ውጤት የሚጠበቅበት ነው፡፡
በእመቤት ሲሳይ