ሠንደቅ ዓላማችን ልዩነቶቻችንን በውበት የሚያስተሳስርና ለጋራ መግባባታችን ትልቁ መገናኛ ነው – አቶ አህመድ ሺዴ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሠንደቅ ዓላማችን የሁላችንም የጋራ ጥላ፣ ልዩነቶቻችንን በውበት የሚያስተሳስርና ለጋራ መግባባታችን ትልቁ መገናኛ ነው አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አህመድ ሺዴ።
19ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተከበረ ነው።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ አፈ ጉባኤው እንዳሉት÷ ሠንደቅ ዓላማ የሀገር ሉዓላዊነት፣ ነፃነት፣ ክብርና አንድነት መገለጫ የሆነ የጋራ ምልክት ነው።
የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር፣ ለሀገርና ለወገን የተከፈለውን መሥዋዕትነት በማሰብ እያንዳንዱ ዜጋ ለሀገሩ ምን መሥዋዕትነት እንደከፈለና ምን ማበርከት እንዳለበት ሊያስብ ይገባል ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማን ማክበር ሀገርን ማክበር፣ ለሀገር የተከፈለውን መሥዋዕትነት ማስታወስ እና ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈውን የጋራ ኃላፊነት ማረጋገጥ እንደሆነም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ሥልጣኔዎች መነሻና ባለቤት መሆኗን የጠቆሙት አፈ ጉባኤው እነዚህ የሥልጣኔ እሴቶች ተደምረው ለነገዋ ኢትዮጵያ ግንባታ ሊውሉ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ለኢትዮጵያ የነበርነው፣ ያለነው እና ወደፊትም የምንኖረው እኛው ነን ያሉት አቶ አህመድ በዚህም ምክንያት በራሷ አቅም የቆመችና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷ የተከበረ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም ዜጋ መነሳት እንዳለበት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት በተለያዩ ቋንቋዎች ባህሎች እና አኗኗር ውስጥ ቢሆኑም በጋራ ታሪክ እና በጋራ ሀገር የተሳሰሩ እንደሆኑም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዘርፎች የለውጥና የዕድገት ጉዞ ላይ እንደምትገኝ የጠቆሙት አፈ ጉባኤው ይህ ጉዞ ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆን የዜጎች ብሔራዊ መግባባትና ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት መገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ሠንደቅ ዓላማችን የሁላችንም የጋራ ጥላ፣ ልዩነቶቻችንን በውበት የሚያስተሳስርና ለጋራ መግባባታችን ትልቁ መገናኛ መሆኑንም አፈ ጉባኤው አስገንዝበዋል።
በእመቤት ሲሳይ