ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ 19ኛው ሠንደቅ ዓላማ ቀንን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት ዋና ዋና ነጥቦች፡- On Oct 12, 2026 10 የአንድነትና የሉዓላዊነት ክብራችን ኃያል መገለጫ በሆነው ሠንደቅ ዓላማችን ስር ተሰባስበን ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን በሚል መሪ ቃል ለምናከብረው 19ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን እንኳን አደረሳችሁ፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር፣ ክብርና ቃልኪዳን በልቡ የሚያድስበት ህብረብሔራዊ ኢትዮጵያዊነትን በጋራ የምናጎለብትበት የነገውን ብሩህ ተስፋችንን የምናበረታበት ታላቅ ብሔራዊ ዕለት ነው፤ ሠንደቅ ዓላማችን የብሔራዊ ህብረታችንና አንድነታችን ማሳያ፣ የዜጎች ሀገራዊ ፍቅርና ሀገራዊ ስሜት መገለጫ ታሪካዊ ማህበራዊ ትስስራችንን እና የስነልቦና አንድነታችንን ማጽኛ ምልክታችን ነው፤ ሠንደቅ ዓላማ የመስዕዋትነት፣ የነጻነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነታችን መለኪያ፤ የሕዝቦች እኩልነትና የህብረታችን ህያው ምስክር ነው፤ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደምና አጥንታቸውን ከስክሰው ውድ የህይወት መስእዋትነት ከፍለው በክብር ያስረከቡን ነው፤ ሠንደቅ ዓላማችን በልባችን ታትሞ የቆየ የአሸናፊነትና የነጻነታችን ዓርማ ነው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ነጻነትና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ታፍራና ተከብራ የቆየች ታላቅ ሀገር ስትሆን፤ የሠንደቅ ዓላማ ታሪኳም እንዲሁ አብሮ ከሀገረ መንግሥት ግንባታዋ ጋር በእጅጉ የተቆራኘና የተሳሰረ ነው፤ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በእኛ ብቻ ሳይሆን በመላው የጥቁር ህዝቦችና በአፍሪካውያን ዘንድ የነጻነት፤ የእኩልነትና የጽናት ተምሳሌት በመሆኑ በርካታ ሀገራት ቀለማቱን የነጻነታቸው ዓርማ አድርገው ወስደውታል፤ እነዚህ ሀገራትና ህዝቦች ተምሳሌታችንን ስለወረሱ ከፍ ያለ ምስጋና ለማቅረብ እሻለሁ፤ ኢትዮጵያችን የባለ ብዙ መልክ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ሀይማኖቶች እንዲሁም በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሀብቶች ሀገር ናት፤ ብዙ ሆና አንድ፤ አንድ ሆና ደግሞ ብዙ ነች፤ የዚህ ሁሉ ውበትና የህብረብሔራዊ ጥንካሬ መገለጫ ደግሞ ይሄው ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማችን ነው፡፡ ሀገራችን በቅርብ ዓመታት የገጠሟትን ከባድ የህልውና ፈተናዎች በህዝቦቿ የተባበረ ክንድ በፅናት ተሻግራ የራሷን ዕድል የመወሰን ብቃቷን እያስመሰከረች ትገኛለች፡፡ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ በመልካም ፈቃዱ 10 Share FacebookTwitterTelegramWhatsAppEmailViberPrint