የህገ ወጡ ሕወሓት ቡድን ጭቆና ማብቃትና የትግራይ ህዝብ አዲስ ተስፋ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን «ጽምዶ» በሚል እኩይ መጠሪያ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ከሚገኙ ባንዳዎች እንዲሁም የውጪ ጠላቶች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ለማፍረስና የህዝቦቿን ሰላም ለማደፍረስ ያጠመደው የጥፋት ሴራ እየከሸፈ ይገኛል፡፡
በትግራይ ክልል የበተለያዩ ከተሞች የሚታየው የሕዝብ ስሜት እና የተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች የዚሁ አዲስ ምዕራፍ ማብሰሪያ ናቸው።
የክልሉ ህዝብ ወደ አደባባይ በመውጣት የሕወሓትን አፋኝና ገዳይ ስርዓት በማውገዝ ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለፌደራል መንግሥቱ ያላቸውን ሙሉ ድጋፍ ገልጸዋል።
በሰልፉ ላይ የተገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ለአስርታት ዓመታት በቡድኑ የጨካኝ አገዛዝ ስር ወጣቶች በግዳጅ ወደ ጦር ሜዳ እየተነዱ የማያልቅ እሳት ውስጥ መቆየታቸውን አውግዟል።
በአፈሳ የወሰዷቸው ህጻናት አልተመለሱም፤ በጣም አስቃቂ ህይወት ነው እየኖርን የነበረው ሲሉ የገለጹት ነዋሪዎቹ የወላድ መሃን ሆነው በሰቀቀን ይኖሩ የነበሩ እናቶች ዛሬ ልጆቻቸውን በሰላም የማሳደግ ተስፋ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን በመፍራት ወጣቱ በየጥሻው ተሸሽጎ የሚያድርበት ወጥቶ መስራት የማይችልበት የጨለማ ጊዜ ማብቃቱን የከተማዋ ወጣቶች በደስታ ገልጸዋል።
የሕገ ወጡ ሕወሓት አመራሮች የራሳቸውን ልጆች በአዲስ አበባ እና በውጭ ሀገራት በቅንጡ ህይወት እያኖሩ የድሃ ልጅ ግን በየጦር ሜዳው እንዲረግፍ ማድረጋቸው የቡድኑን እውነተኛ የደም ነጋዴነት ባህሪ ያሳየ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።
ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን ከኢትዮጵያዊነት ማንነታቸው የመገንጠልና ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማውን «ጽምዶ» በሚል ሽፋን ለማስፈጸም የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ እንደሚቃወሙት አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በከተማዋ ለዓመታት ምንም ዓይነት የመሰረተ ልማት፣ የውሃና የመብራት አገልግሎት ሳይሟላ ህዝቡ በችግር እንዲማቅቅ መደረጉን የጠቀሱት ነዋሪዎች፤ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በእኩልነት የመልማት፣ የመበልጸግ እና በሰላም የመኖር ፍላጎት እንዳለውም አሳውቀዋል።
ይህ ህዝብ የሚፈልገው ልማትና ሰላም ብቻ ነው፤ መሪያችን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ናቸው በማለት ያላቸውን ጽኑ የሀገራዊነት አቋም አሳይተዋል።
አሁን ላይ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ሰላምና መረጋጋት ተመልሶ ህዝቡ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቱን አግኝቷል። ይህ የነጻነትና የሰላም ጭላንጭል እና የክልሉ ሕዝብ ያሳየው ድጋፍ አፋኙ የሕወሓት ሕገ ወጥ ቡድን የህዝብ መሰረት እንደሌለው ማሳያ ነው።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በዮናስ ጌትነት