የመደመር መንግሥት የጉዞ ትልም ለኢትዮጵያ ከፍታ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሊቨሪ ክትትል ዘርፍ ኃላፊ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‘የትርክት ዕዳና በረከት’ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ የተለያዩ ሥልጣኔዎችን በተለያዩ አካባቢዎችና በተለያዩ ዘመናት ያስተናገደችው ኢትዮጵያ፤ በዘመን ጅማሬ የደመቀና ገናናው ሥርዓት ሃልዮታዊ ማሕቀፍን መቀየር ባለመቻሉ የመንግሥታት ገናናነት በየዘመናቱ እየኮሰመነ የማኅበረሰቡም ኑሮ እየወየበ እንዲመጣ ምክንያት ሆነ ሲሉ ያብራራሉ።
ሕጸጽ በበዛባቸውና በዋናነትም ከውጭ በተኮረጁ አስተሳሰቦች ለመምራት በተደረገው ጥረት፣ ኢትዮጵያ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ስትናጥ መቆየቷን በማስታወስ፤ መሪዎቿ ለሕመሟ የማይሆን መድኃኒት እየጋቷት ተፈራርቀዋል በማለት ይገልጻሉ፡፡
“… ያልተገባው መድኃኒት ሌላ ሕመም እያመጣበት ስትሰቃይ ኖራለችና፡፡ ከጭንቅና ከመከራ ለመገላገለል በፈለገችበት ወቅት ተገቢውን መድኃኒት አግኝታ አታውቅም፡፡ የወሰደችው እያገረሸባት ወይም ተጨማሪ ሕመም እየፈጠረባት ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡
“መደመር ለምን? ለምን አሁን አስፈለገን? ብለን እንጠይቅ፡፡ የተቃርኖ ትርክቶቻችን ዕዳን እንጂ በረከትን ሊያወርሱን አልቻሉም፡፡ የተውሶ ትርክቶቻችን ለነጠላ ቡድናዊ ፍላጎት ጥቅም አስጠበቁ እንጂ ለጋራ ሀገራዊ ልዕልናችን አልጠቀሙንም፡፡
የተውሶ ዕሳቤዎች የትውልዶችን ዕዳ ከማራዘም የዘለለ ፋይዳ አላመጡም፡፡ አስተሣሣሪ ታሪክና ሥልጣኔ ቢኖረንም አስተሣሣሪ ትርክት ጠፍቶ ደም አፋሳሽ ሀገር አፍራሽ ትርክቶች ዋጋ አስከፈሉን፡፡
አዲስ አስተሳሰብ፤ አዲስ መንገድ፤ አዲስ ትርክት አስፈለገ፡፡ መደመር ተወለደ፡፡ ተነጣጥለን ወድቀናል፡፡ ተደምረን የትርክትን ዕዳ በትርክት በረከት ለመቀየር መደመር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የግድ ነው፡፡” ሲሉ በመጽሐፋቸው ገጽ 522-523 ላይ አስፍረዋል።
የመደመር መንግሥት እሳቤ ያለፉትን አዎንታዊ እሴቶች በማስቀጠል፣ ስህተቶችን በማረም እና የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ለማድረግ አዳዲስ እይታዎችንና አሰራሮችን ማካተት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ይህ አስተሳሰብ ወደ ተግባር ሲቀየር በሀገሪቱ የልማት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚይዙ፣ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጡ ግዙፍ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በመደመር መንግሥት ከተከናወኑት አበይት ተግባራት መካከል አንዱ ለዓመታት ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የቆዩ ወይም የታቀዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ወደ ፍፃሜ ማድረስ እና አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን መገንባትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከተሞችን ለማዘመን፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓትን ለማስፋፋት፣ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ፣ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እንዲሁም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በመደመር መንግሥት የተወሰዱ ርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል።
ይህም ኢትዮጵያን ወደኋላ ሲጎትታት ከነበረው የተናጠል ጉዞ በማላቀቅ በተደመረ አቅም የወደፊት ጉዞዋን እንድትቀጥል መንገድ ከፍቷል።
ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገበውን የኢትዮጵያ የታላቅነት ጉዞ በመደመር ታላቁ ስትራቴጂ በመመራት በማስቀጠል የኢትዮጵያን ከፍታ የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በመደመር መንግሥት የተጀመረው የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ወደ ከፍታ የሚወስዳት መሆኗን ያረጋገጠ ሲሆን፤ የተከናወኑት ግዙፍ ሥራዎች ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ከፍታዋን እንድትቆናጠጥ መሰረትን የጣሉ እንዲሁም ለወደፊቱ ትውልድ ጠንካራ ሀገር ለማሻገር ያለውን ተስፋ እያለመለሙ የሚገኙ ስኬቶች ናቸው፡፡