Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም አጋርነታቸውን ለማጠናከር መከሩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተውን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
5ኛ ቀኑን በያዘው እና በታይላንድ ባንኮክ እየተካሄደ በሚገኘው የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በስብሰባው ላይ እየተሳተፈ ነው።
በዚህም በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ልዑክ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ ልማትና የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ክርስቲ ማክኔል ጋር ውይይት አድርጓል።
ውይይቱ በወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች እና ኢትዮጵያ ዘላቂ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት እንዲሁም የረጅም ጊዜ እድገትን ለማረጋገጥ የቅድሚያ ትኩረት በሰጠቻቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
በተጨማሪም ውይይቱ አሁን ባሉ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ላይ ሀሳብ ለመለዋወጥ ምቹ አጋጣሚን የፈጠረ መሆኑ ተገልጿል።
የዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ ልማትና የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ክርስቲ ማክኔል በዚህ ወቅት÷ ኢትዮጵያ በመርህ ላይ ተመስርታ እያከናወነች ያለችውን ጥረት አድንቀዋል።
ሀገሪቱ ለቀጣናዊ ሰላም፣ መረጋጋት እና ልማት እያበረከተች ያለውን ስትራቴጂካዊ አስተዋጽኦ አንስተው ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያላትን ጽኑ አቋም አረጋግጠዋል።
ሁለቱም ወገኖች ገንቢ ውይይቶቻቸውን አጠናክረው ለመቀጠል እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተውን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.