የግብፅ ፍላጎት የውኃ ደኅንነት ጉዳይ ሳይሆን የጂኦፖለቲካዊ የኃይል ሚዛን ጉዳይ ነው – አለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብፅ ፍላጎት የውኃ ደኅንነት ጉዳይ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባሕር አካባቢ ያለውን ጂኦፖለቲካዊ የኃይል ሚዛን የሚመለከት ነው አሉ የፖለቲካ ሳይንቲስትና ጠበቃ አለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር)።
አለማየሁ (ፕ/ር) እንዳሉት÷ ግብፅ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳታገኝ የምታደርገው ተቃውሞ የሀገሪቷን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለመገደብና እያደገ የመጣውን የቀጣናዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሚና ለማዳከም የተዘጋጀ ስትራቴጂክ ነው፡፡
ግብፅ በኢትዮጵያና በዓባይ ተፋሰስ ላይ ያላት ፍላጎት ከ1820ዎቹ ዓመታት ጀምሮ እንደሆነ ገልጸው በወቅቱ ግብፅ በዓባይ ላይ ቁጥጥሯን ለማስፋት በማሰብ በሱዳን በኩል ወታደሮችን ልካ የነበረ ቢሆንም ጥረቷ አለመሳካቱን አውስተዋል።
ግብፅ በመቀጠል በ1875 እና 1876 በኢትዮጵያ ላይ ታላላቅ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታ በጉንደትና በጉራ ጦርነቶች ተሸንፋ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።
የግብፅ ፍላጎት የውኃ ደኅንነት ጉዳይ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባሕር አካባቢ ያለውን ጂኦፖለቲካዊ የኃይል ሚዛን የሚመለከት እንደሆነም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ጥንካሬ ለአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን ጠቅሰው ይህም ዓለም አቀፍ የንግድ ግንኙነቷን የሚያሰፋና ቀጣናዊ ኃያልነቷን የሚያሳድግ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ÷ የኢትዮጵያን ወደ ቀይ ባህር መቅረብና የባህር በር መልሶ የማግኘት ጥረት ግብጽ እንዳይሳካ እየሞከረች ነው።
ግብፅ የኢትዮጵያን ወደ ቀይ ባሕር መቃረብ መቃወሟና በዓባይ ውሃ ላይ ያላት አቋም እርስ በርስ የተሳሰሩ ብሎም የኢትዮጵያን ልማትና ቀጣናዊ ተፅዕኖ ለመገደብ የሚደረግ ሰፊ ጥረት አካል መሆኑንም አመልክተዋል።