Fana: At a Speed of Life!

የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግርን በተግባር ያረጋገጠው አየር ኃይል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመደመር መንግሥት ሥር ነቀል ሪፎርም የጎለበተው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅም እና እና የሉዓላዊነት አስተማማኝ ዘብ ሆኗል።
የሠራዊቱ አንድ አካል የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የነበረውን ታሪካዊ ቀዳሚነት፣ አሁን ካለው ፈጣን የቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር በማቀናጀት አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
አየር ኃይሉ የታሪክ ኩራት ብቻ ሳይሆን የዘመናዊነት ተምሳሌት መሆኑን በተግባር አረጋግጧል። የሌሎችን እጅ ከመጠበቅ ተላቆ ራሱን ወደመቻል ተሸጋግሯል።
አየር ኃይሉ በገነባቸው ከባድና ቀላል የጥገና ማዕከላት አማካኝነት ተዋጊ የጦር ጄቶችን፣ የትራንስፖርትና የውጊያ ሄሊኮፕተሮችን፤ የተለያዩ የማሰልጠኛ አውሮፕላኖችን የመጠገን፣ የማሻሻልና የማዘመን ሙሉ አቅም ፈጥሯል።
ይህ ስኬት የውጭ ምንዛሪ ወጪን ከመቆጠቡም በላይ፣ የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ሽግግርን በተግባር ያረጋገጠ ታላቅ ብሔራዊ ድል ነው። በዚህም የጥራትና የብቃት መለኪያውን ወደ ላቀ ደረጃ አሳድጓል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የቅርብ ጊዜ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ የሱ-30 ባለ ብዙ ሚና ተዋጊ ጄቶችን በመታጠቅ፣ የአየር ላይ የመምታት አቅሙን በማይደፈር የልዕልና ደረጃ ላይ አድርሷል።
እነዚህ ጄቶች በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታና የአየር ንብረት ውስጥ ተልዕኮን የመወጣት ልዩ ብቃት ያላቸው የቴክኖሎጂ ጥበቦች መሆናቸውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል።
ይህም የሰማይ ላይ ጀግኖችን በላቀ ዲሲፕሊንና በረቀቀ ቴክኖሎጂ ለማፍራት ያስቻለ የጥራት መሠረት ጥሏል።
አየር ኃይሉ የታጠቃቸው ቴክኖሎጂዎች ጠላትን ከሩቅ ርቀት የመለየትና እንቅስቃሴውን በንቃት የመከታተል አቅም ያለው በመሆኑ፣ ለአየር ኃይላችን የማይተኛ የሰማይ ላይ ዐይን ሆኖ ያገለግላል።
የዘመኑ የአየር ላይ ውጊያ ከበረራና ከፍንዳታ ባለፈ፣ በረቀቀ የኤሌክትሮኒክስ ፍልሚያ ላይ የተመሰረተ ነው። አየር ኃይሉ በዚህ ረገድ ያለውን ቁመና በማፈርጠምና የጠላትን የቴክኖሎጂ የበላይነትና የጥቃት ዝግጅት አስቀድሞ በማምከን፣ የጦርነቱን የኃይል ሚዛን ወደ ወገን የመመለስ ልዩ አቅም ፈጥሯል።
በተጨማሪም አየር ኃይል ዘመናዊ መሣሪያ ያለ ዕውቀት ፋይዳው አነስተኛ ነው የሚለውን መርህ በመከተል፣ የሪፎርሙ ልብ የሰው ኃይል ግንባታ ላይ አርፏል።
በዚህም አብራሪዎችን፣ የጥገና መሐንዲሶችንና የቴክኒክ ባለሙያዎችን በከፍተኛ ጥራት በማሰልጠን የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
በሌላ በኩልም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገነቡ ሰፋፊ የውጊያና የሎጂስቲክስ መሠረተ-ልማቶች፣ ተቋሙ ፈጣን ተንቀሳቃሽነትን በተግባር እንዲያረጋግጥ አስችለውታል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ የጀግንነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት የመራመድ፣ የመታደስና የቴክኖሎጂ ባለቤት የመሆን ታሪክም ጭምር ነው።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.