Fana: At a Speed of Life!

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያሳየውን ሰብዓዊነትና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንደግፋለን – ዓለም አቀፍ ወታደራዊ አታሼዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያሳየውን ሰብዓዊነት እንደግፋለን አሉ የዓለም አቀፍ ወታደራዊ አታሼዎች ፡፡

ለተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼ አባላት በቢሾፍቱ አየር ኃይል ቤዝ በኢትዮጵያ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

ከለጻው በኋላ አታሼዎቹ በሰጡት አስተያየት÷ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ያልተረጋገጡ እና የተሳሳቱ መረጃዎች ሲሰራጩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ዓለም አቀፉን የዲፕሎማቲክ እና የወታደራዊ አታሼ ማኅበረሰብ በመጋበዝ የሰጠው ይፋዊ እና ቀጥተኛ ገለጻ ክፍተቶችን በመድፈን ትክክለኛውንና ወቅታዊውን መረጃ ለማግኘት ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

የእንግሊዝ፣ የአውስትራሊያ፣ የባንግላዴሽ፣ የኬንያ፣ የጋቦን፣ የደቡብ ሱዳንና የታንዛኒያ ወታደራዊ አታሼዎች በሰጡት አስተያየት÷ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ግዴታዋን በመወጣት የሀገሯን ሉዓላዊነት፣ የድንበር አንድነት እና የዜጎቿን ደኅንነት የማስከበር ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብት ያላት መሆኑን አረጋግጠዋል።

የባንግላዴሽ እና የታንዛኒያ ወታደራዊ አታሼዎች በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዓለም አቀፍ የጦር ሕጎችን እና ሰብዓዊ መብቶችን ጠብቆ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሠራዊቱ የንጹሐን ዜጎችን ሕይወት መጠበቅ እና ሕጋዊ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት በቀጥታ ለጎረቤት ሀገራት እና ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ የኬንያ እና የደቡብ ሱዳን ተወካዮች ናቸው፡፡

ዓለም አቀፍ ወታደራዊ አታሼዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጀመረው የሰላም እና የፀጥታ ማስከበር ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘላቂ መረጋጋትን እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸው ÷ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ለምታደርገው የሰላም ጥረት ከጎኗ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.